ኀዳር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሲሞክሩ ማላዊ ላይ ተይዘው በእስር ቤት ውስጥ ሲንገላቱ የነበሩትን ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በሰጡት 9 ሺ የአሜሪካ ዶላር ቁጥራቸው 223 የሚሆኑትን በቻርተር አውሮፕላን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጓል።
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅቱ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ያደረገ ሲሆን እስካሁን ድረስ አጠቃላይ ድምራቸው 387 ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን መመለሱን ድርጅቱ አስታውቋል።
በማላዊ በተለያዩ እስርቤቶች ውስጥ የነበሩት ስደተኞች ከ2 እስከ 9 ወራት በተጨናነቀ ሁኔታ ታስረው የቆዩና የተለያዩ በደልና ሰቆቃዎች ሲፈጸምባቸው የነበሩ ሲሆን ከእስራቱ በተጨማሪም በሕገወጥ መንገድ አገር በመግባት ወንጀል ተከሰው በፍርድ ቤት 35 የአሜሪካ ዶላር መቀጮ ተበይኖባቸው እንዲከፍሉ ተደርገዋል።
ድርጅቱ ከአሜሪካም ወደ አገራቸው ለመመለስ ፍቃደኛ የሆኑ 164 ኢትዮጵያዊያንን መመለሱንና አሁንም ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ስራ ፍለጋ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት መፍለስ መቀጠላቸውንና አብዛሃኞቹ በታንዛኒያ፣ሞዛምቢክ፣ማላዊ እንግልትና ሰቆቃ እንደሚፈጸምባቸው ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOMን ጠቅሶ ኒውስ ሃወር ዘግቧል።