ኢሳት (ጥር 4 ፥ 2009))
በሶስት ክልሎች አዲስ የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ ወደ 200 አካባቢ የሚጠጉ ወረዳዎች በአንደኛ ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉ ሆነው መለየታቸውን የተባበሩት መንግስት ድርጅት አስታወቀ።
የድርቁ አደጋ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የገለጸው ድርጅቱ ባለፈው አመት በተመሳሳይ ደረጃ ውስጥ ተመድበው የነበሩት ወረዳዎች በድጋሚ አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ተረጂ መሆናቸውን በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።
በኦሮሚያ፣ ሶማሊ እና የደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ በአንደኛው ደረጃ የተፈረጁት አብዛኞቹ ወረዳዎች በደቡብ ክልል የምስራቅ አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።
ከመስከረም እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ መጣል የነበረበት ዝናብ በወቅቱ ባለመጣሉ ምክንያት በሶስቱ ክልሎች አዲሱ የድርቅ አደጋ መከሰቱ ይታወሳል። በቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌ እና ምስራቅ ሃረርጌ ዞን የሚገኙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ዘጠኙም የሶማሊያ ክልል ዞኖች እንዲሁም የኦሞ፣ ጋሞ ጎፋ፣ እና የሰገን የደቡብ ዞኖች በአዲሱ ድርቅ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ተመልክቷል።
ይህንኑ የድርቅ አደጋ ለመከላከል 922 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድርቁ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።
ድርቁን ለመታደግ የሚያስፈልገው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ተቀራራቢ ሆኖ የተገኘ ሲሆን፣ ወደስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውም ታውቋል።
በሃገር ውስጥና በውጭ ያሉ አለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ድርቁ የከፋ አደጋን ከማድረሱ በፊት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳስቧል።
ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች ተከስቶ የነበረው የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ባላገኘበት ወቅት አዲስ የድርቅ አደጋ ዳግም መከሰቱ ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ አስቸጋሪ መሆኑን የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።