ጥቅምት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ገዳሪፍ አቅራቢያ በተቀሰቀሰ ውጊያ 16 ሱዳናዊያን መገደላቸውን፣ 12 መቁሰላቸውን እንዲሁም 7ቱ ታግተው መወሰዳቸውንና የደረሱበት እንደማይታወቅ ከ300 በላይ የቁም ከብቶችም መዘረፉን የቀድሞው የአገሪቱ ጦር አዛዥና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ለፓርላማ ሪፖርት አቅርበዋል።
ኢስማት አብዱረሕማን ” ሽፍቶች” ያሉዋቸው መሬታችንን አሳልፈን አንሰጥም ያሉ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ለፓርላማው ከተናገሩ በሁዋላ፣ የፓርላማ አባላቱ በመልሱ በአካባቢው የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት በብዛት እንዲሰፍርና በሱዳናውያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲያስቆም ጠይቀዋል።የገዳሪፍ አካባቢ የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ኢስማኤል አህመድ ሙሳ በበኩላቸው ከ794 ኪሎ ሜትር በላይ የሆነ መሬት የኢትዮጵያ ገበሬዎች በኃይል ወስደውብናል በማለት ለፓርላማው ተናግረዋል።
የኢህአዴግ መንግስት ሰፊ የሆነ ለም መሬት ለሱዳን አሳልፎ ከሰጠ በሁዋላ፣ በኢትዮጵያ አርሶአደሮችና በሱዳን ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ ጊዜዎች ግጭቶች ተከስተው ከሁለቱም ወገን ሰዎች አልቀዋል። ቀድም ብሎ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሱዳን ድረስ በመሄድ “ድንበሩ በቅርቡ እንደገና ይካለላል” በማለት ተናግረው የነበሩ ቢሆንም፣ የድንበር ከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን ተቃውሞ በመፍራት እስካሁን ተግባራዊ አላደረጉትም። ሱዳኖችም በየጊዜው ” አለን የሚሉት መሬት እንዲሰጣቸው የኢህአዴግን መንግስት እየጠየቁ ነው። የአካባቢው አርሶደሮች በበኩላቸው ” ሱዳን እንኳንስ ተጨማሪ መሬት ሊገባት፣ ከኢህአዴግ በገጸ በረከት የተበረከተላትን መሬት ካልመለሰች ግጭቱ አይቆምም” ይላሉ።
በቅርቡ የሱዳን ታጣቂዎች ስምንት ኢትዮጵያዊያንን ስራ ትቀጠራላችሁ በሚል አታለው በመውሰድ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል።
ሱዳን ከኢህአዴግ መንግስት ጋር በቅርበት በመስራት ፣ የኢህአዴግን አገዛዝ የሚቃወሙትንና በአገሯ ስደት የጠየቁ በርካታ ኢትዮጰያውያንን አሳልፋ ሰጥታለች።