16 ኢትዮጵያውያንን አይሲስ ገደለ በሚል የተሰራጨውን ያልተረጋገጠ ዜና ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ሃዘኑን ገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 4 ፥ 2008)

አይሲስ የተባለው አለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን 16 ኢትዮጵያውያንን ገደለ በሚል የተሰራጨው ዜና አልተረጋገጠም። ኢሳት ባደረገው ማጣራት የዜና ቀዳሚ ምንጭ የሆነው የኢራኑ ፕሬስ ቲቪ ያሰራጨውን ዜና ከድረ-ገጹ አንስቷል። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት ይህንኑ ምንጭ በመጥቀስ ሃዘኑን መግለጹን ለመረዳት ተችሏል።

በተለያዩ ድረገጾችና በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የተሰራጨው ይኸው ኢትዮጵያውያን ተገደሉ የሚለው ዜና፣ ከአመት በፊት የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውስ እንጂ አዲስ ክስተት አለመሆኑን መረዳት ተችሏል።

በወቅቱ የኢትዮጵያውያኑ መገደል ተከትሎ ዝምታን የመረጠውና ዜግነታቸው አልተጣራም በማለት ሃዘኑን ለመግለጽ ተቆጥቦ የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት አሁን አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሃዘኑን ገልጿል። ሆኖም የሃዘን መግለጫው ባልተጨበጠ መረጃ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ያልተረጋገጠውንና የዜና ምንጩ ያስወገደውን ዜና በተመለከተ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው መግለጫ ሰጥተዋል።