ኢሳት (የካቲት 28 ፥ 2008)
በአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄን ለመሳተፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጋችኋል የተባሉ 13 ሰዎች የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።
ከአራት ወር በፊት ከአርባ ምንጭ ከተማ በጸጥታ ሃይሎች ተይዘው ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ የተደረጉት እነዚሁ ተከሳሾች የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ እንደሆነ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ክሱን ሰዎች ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው አቃቤ ህግ ተከሳሾች መቀመጫውን በኤርትራ ካደረገው የአርበኞች ግንቦት 7 ጋር በአባልነት ለመታቀፍና የሽብር ድርጊትን ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል ሲሉ በክሱ አቅርቧል።
ይሁንና ተከሳሾች ለአራት ወራቶች ያህል ክስ ሳይመሰረባቸው ለምን እንደቆዩ ፖሊስ የሰጠው ምላሽ አለመኖሩ ታውቋል።
ነዋሪነታቸው በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ የሆነ ኣነዚሁ ተከሳሾች በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ምርመራዎች ሲካሄድባቸው መቆየትን ከሃገር ቤት ከተገነው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ከተከሳሾች መካከል በጋሞጎፋ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አደራጅ የሆኑት አቶ ሉሉ መሰለ የሚገኙበት ሲሆን፣ ክሱን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ለቀጣዩ ወር አጋማሽ ተለዋጭ ቀጠሮን ሰጥቷል።