121 ኛው የዐድዋ ድል በአል ተከበረ

የካቲት ፳፫ ( ሃያ ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያውያን አርበኞች ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ ሃይላቸውን አሰባስበው የመጡትን የጣሊያን ወራሪዎች አድዋ ላይ ድል ያደረጉበት 121ኛው የነጻነት ቀን ተከብሮ ውሎአል።
በዳግማዊ አፄ ሚኒልክ እና በባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል የተመራው ፣ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴንና ራስ አሉላ አባነጋን እና ሌሎችንም ሰመ ጥር ጅግኖችን ያሳተፈው ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በድል ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የነጭ የበላይነት አምርረው ሲታገሉ የነበሩትን የጥቁር የሰው ዘሮች በሙሉ ያስፈነደቀ ነበር። በንቀት ይታዩ የነበሩት ጥቁር የሰው ዘሮች፣ በነጮች ላይ ድል ያደረጉበት የመጀመሪያው ክስተት ተደርጎ የተቆጠረው አድዋ፣ ቅኝ ገዢዎች የኢትዮጵያንን ህልውና ተገደው እንዲቀበሉ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
የህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝ ላለፉት ሩብ ክፍለዘመናት በአሉን ከገዥው ፓርቲ አመታዊ በአል ባነሰ መልኩ እንዲከበር በማድረግ የዐድዋ ድልን ለማደብዘዝ የተለያዩ ስራዎች ሲሰራ ከቆየ በሁዋላ፣ በአገር ውስጥ የሚደርስበትን ተቃውሞ ለማብረድ ይረዳኝ ይሆናል ብሎ በማሰብ የዘንድሮው የዐድዋ ድል መታሰቢያ ትኩረት ሰጥቶ አክብሯል።