12 ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ አስገቡ

ጥቅምት ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲዎቹ በደብዳቤያቸው ከዚህ ቀደም ያቀረቡዋቸው ጥያቄዎች መልስ ባለማግኘታቸውና ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጡ በመስጋታቸው ደብዳቤ ለመጻፍ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው “የፖለቲካ አመራሮችን ማስፈራራት፣ የአካላዊ ጉዳት ማድረስ፣ በሃሰት ውንጀላና የፈጠራ ክስ ማሰር እየተጠናከረ መምጣት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙና አላማቸውን ፣ፕሮግራማቸውንና አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን ለህዝብ እንዳያቀርቡ ማድረግ፣

ገዢው ፓርቲ መንግስታዊ መዋቅርን በመጠቀም የምርጫ ቅስቀሳ እየዳረገ መሆኑን፣ ገዢው ፓርቲ ከመንግስት ካዝና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ተቀብሎ ለሚፈልጋቸው ፓርቲዎች በማከፋፈል በፓርቲዎች መካከል አላስፈላጊ የአቅም ልዩነት በፈጠረበትና የጥቅም ትስስር ደጋፍ እየገዛ መሆኑ፣

የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች፣ ጸሃፊዎችንና አሳታሚዎችን በመክሰስ ለወይኒ ወይም ለስደት በመዳረግ መራቹ ህዝብ አማራጭ የማግኘት መብቱ እንዲገደብ ማድረጉ፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ የሚታዩት ግጭቶችን ተከትሎ የሚታየው የህይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደም፣ መፈናቀልና

ማህበራዊ ምስቅልቅል አሳሳቢ መሆኑ በግልጽ የሚታይና በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለ እውነታ ” መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፓርቲዎቹ ከዚህ ቀደም ” ከ2005 ዓም እስከዛሬ ያቀረቡዋቸው ጥያቄዎች እንዲመለሱ፣ ገዢው ፓርቲ   በጋራ ተገናኝተው በምርጫና የመድበለ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚወያዩበት የጋራ መድረክ እንዲዘጋጅ” ጠይቀዋል።

እነዚህ ጥያቄዎች ባልተመለሱበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ተሳትፎ ለኢህገመንግስታዊነትና ለኢዲሞክራሲያዊነት እውቅና በመስጠት አገሪቷንና ህዝቡን ወደባሰ አዘቅት መወርወር ነው ሲል የድርጅቶች መግለጫ ጠቅሷል።