መስከረም ፪(ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጋሞጎፋ ዞን በቁጫ ወረዳ በቅርቡ የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ መርታችሁዋል በሚል የታሰሩ የወረዳዋ አገር ሽማግሌዎች እና ነዋሪዎች ማስረጃ በመጥፋቱ እንዲፈቱ ፍርድ ቤት ሀምሌ 22 እና 30 ቢወስንም ፖሊስ የፍርድ ቤትን ትእዛዝ አልቀበልም በማለት ግለሰቦቹ እስከሁን ድረስ ታስረው እንደሚገኙ ታውቋል።
ፖሊስ ከፍርድ ቤት በላይ ሆኖ እስረኞችን አልፈታም ማለቱ እና እንዲያውም ሌሎች ተጨማሪ ሰዎችን ለማሰር በዝግጅት ላይ መሆኑ የአካባቢውን ሰው እያነጋገረ ይገኛል።
ከሳምንታት በፊት ወደ ጠቅላይ ሚ/ሩ ቢሮ ያቀኑ ወደ 60 የሚጠጉ የወረዳዋ የአገር ሽማግሌዎች የታሰሩት ግልሰቦች እንዲፈቱና እስርና እንግልቱ እንዲቆም ጥያቄ ቢያቀርቡም ከተስፋ በስተቀር እስካሁን ድረስ ተጨባጭ መልስ አላገኙም።
አካባቢው ነዋረዎች የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የሚወስዱት የአፈና እርምጃ በአካባቢው ዳግም ግጭት እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል በማለት ያስጠነቅቃሉ።
በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳውን የፖሊስ አዛዥ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።