ፕ/ት አቦማ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ለሰብአዊ መብት ቦታ እንዲሰጡ አንድ ሴናተር ጠየቁ

ሐምሌ ፲፮ (አስራስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ጥያቄውን ያቀረቡት በአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ግንኙነት የተዘዋዋሪ ወንጀሎችና የሕዝብ ደሕንነት ሊቀመንበር የሆኑት ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ናቸው።
ዴሞክራሲ፣የሰብዓዊ መብትና ዓለምአቀፍ የሴቶች ጉዳይ፣ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት ቅድሚያ ሊሰጡባቸው የሚገቡ አንገብጋቢ ጉዳዮች መሆናቸውን ሴናተሩ ጠቅሰዋል።
ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ”ኢትዮጵያና አሜሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋት በአካባቢው መረጋጋትን ለመፍጠር ፍላጎት ማሳየታቸውም አስፈላጊ ቢሆንም፤አሜሪካ የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተንሸዋረረ ዕይታ ማየት ግን የለባትም” ብለዋል።
”የፖለቲካ ምኅዳሩን በመዝጋት ሲቪክ ማኅበራት፣መገናኛ ብዙሃን፣ፖለቲከኞች እንዳይንቀሳቀሱ በማሽመድመድ የኢትዮጵያ መንግስት ችግሮች ላይ ነዳጅ እየጨመረ እያባባሰ ነው ይህም ለቀጣይ በአገሪቱ መረጋጋት እንዳይፈጠር እያደረገ ነው።” ሲሉ ሴናተሩ አክለዋል።
ሴናተሩ ”በኢትዮጵያ ጉብኝትዎ ወቅት ለባለስልጣናቱ እንዲነግሩልኝ የማሳስብዎት የፖለቲካ እስርን አበክረው እንዲያወግዙ፣ ገዥዎቹ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩና በነጻ የመደራጀትን መብት እንዲፈቅዱ ነው ” ሲሉ ለፕ/ት ኦባማ ጥሪ አቅርበዋል።