(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 5/2010) ታዋቂው ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ስቴፈን ሆውኪንግ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
በወጣትነት ዕድሜያቸው በደረሰባቸው አደጋ በህይወት የሚቆዩት ለሁለት ዓመታት ብቻ እንደሆነ ቢነገራቸውም ታላላቅ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለዓለም እያበረከቱ ተጨማሪ 50 ዓመታትን በዚህች መድር ላይ የኖሩት ስቴፈን ሃውኪንግ ረቡዕ ማለዳ በካምብሪጅ ብሪታኒያ በ76 ዓመታቸው በመኖሪያ ቤታቸው ህይወታቸው አልፏል።
የዘመናችን ምርጥ ሳይንቲስት እና የምጡቅ አእምሮ ባለቤት እንደሆኑ የተመሰከረላቸው ፕሮፌሰር ስቴፈን ሃውኪንግ የ22 ዓመት ወጣት እያሉ በገጠማቸው የአዕምሮና ስፓይናል ኮርድ የነርቭ ህመም (ሞተር ኒውሮን ዲዚዝ) ምክንያት በህይወት መቆየት የሚችሉት ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ብቻ እንደሆነ በሃኪሞች ተነግሯቸው ነበር።
ነገር ግን ስቴፈን ሃውኪንግ ለተጨማሪ 54 ዓመታት ታላላቅ ተግባራትን እየከወኑ መቆየታቸውን ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ እያሉ ከደረጃ ላይ መውደቃቸው ደግሞ ለህመማቸው መባባስ አስተዋጾ ማድረጉም ተመልክቷል።
በሽታው ቀስበቀስ የመናገር ችሎታቸውን እየገደበው ፣መራመድም ተስኗቸው በዊልቸር ለመሄድ የተገደዱት ፕሮፌሰር ስቴፈን ሆውኪንግ በኮምፒውተር እየታገዙ ፣የኮምፒውተሩን መጠቆሚያ (ማውስ) በጉንጫቸው እያንቀሳቀሱ ታላላቅ ተግባራትን ከውነዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1988 ኤ ብሪፍ ሂስትሪ ኦፍ ታይም ( A Brief History of Time) በሚል ያሳተሙት መጽሃፍ ከ 10 ሚሊዮን በላይ ኮፒ የተሸጠላቸው ታላቁ ሳይንቲስት ስቴፈን ሃውኪንግ በአጠቃላይ ከ 15 በላይ የሳይንስ መጽሃፍትን በግል እና በጋራ አሳትመዋል።
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስተር ቴረሳ ሜይ ህልፈታቸውን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ብሩህ እና ምጡቅ አዕምሮ የነበረው ሲሉ ሳይንቲስቱን ስቴፈን ሃውኪንግን አውደሰዋል።
በ22 አመታቸው ቢበዛ በ24 ዓመታቸው እንደሚሞቱ የተነገራቸውና በስኬት 76 ዓመታት የኖሩት ብሪታኒያዊው ሳይንቲስት ስቴፈን ሆውኪንግ ኦምና በአንድ መድረክ ሲናገሩ “ 75 ዓመታት በሕይወት ኖራለሁ ብዬ አልገመትኩም፥በሕይወት ዘመኔም አሻራዬን በመተዌ ዕድለኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል” ብለዋል።
ስቴፈን ሆውኪንግ የሶስት ልጆች አባት ነበሩ።