ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ 250 ዳኞችን ከስራ አባረሩ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 9/2010) የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ 250 ዳኞችን በሙስናና ከትምህርት ማስረጃ ጋር በታያያዘ አባረሩ።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመሪነት መንበር አባታቸውን ሎራን ካቢላን ተክተው የያዙት ጆሴፍ ካቢላ ከአመታት በፊት በተመሳሳይ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ዳኞችን አባረዋል።

ወደ 80 ሚሊየን ሕዝብ የሚኖርባትና በማዕድን ሃብት የበለጸገችው ሐገር መሪ ጆሴፍ ካቢላ በሰጡት ትዕዛዝ በአጠቃላይ 256 ዳኞች ተባረዋል።

የተባረሩት ዳኞች በከፊል የሕግ ዲግሪ ስለሌላቸው የተቀሩትም በሙስና በመሰማራታቸው መሆኑም ተመልክቷል።

ሁለት ዳኞች ደግሞ ራሳቸው መልቀቂያ አቅርበዋል።

የሃገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ታምቡ ምዎምባ የ256ቱን ዳኞች መባረር አረጋግጠዋል።

“ማንኛውም ሰው ወደ ዳኝነት ስራ ሲገባ ገንዘብ ለመሰብሰብ መሆን የለበትም”በማለት የፍትሕ ስርአቱ ያለበትን ችግር አስረድተዋል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዳኞችን በጅምላ የማባረሩ ርምጃ ከ9 አመታት በፊትም መፈጸሙን ለማወቅ ተችሏል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2009 በተመሳሳይ 96 ዳኞች ተባረዋል።