ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ አስመራ ተመለሱ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 9/2010)ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሶስት ቀናት ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ወደ አስመራ ተመለሱ።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ የአዲስ አበባውን የኤርትራ ኤምባሲ በይፋ እንደገና መክፈታቸውም ታውቋል።

በአዲስ አበባና በሃዋሳ ጎዳናዎች ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸውና በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው ስነስርአት ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ አስመራ ሲመለሱ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።

ቅዳሜ ማለዳ ከ20 አመታት በኋላ አዲስ አበባ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ በኢዮቤልዩ ቤተመንግስት እንዲሁም በሃዋሳና በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እንደተናገሩት ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ የተደረገው አቀባበል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያልታየና ደማቅ ነበር።

ላለፉት 27 አመታት በየትኛውም መንግስታዊ መድረኮች ላይ ታይተው የማይታወቁ ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጭምር በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ተቀብለዋል።

ፕሬዝዳትን ኢሳያስ አፈወርቄ በሚሊኒየም አዳራሽ በአማርኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር ፍቅራችንንና ስምምነታችንን ለማወክ የሚፈልጉትን ጨርሶ አንፈቅድላቸውም ብለዋል።

“ክብር ለኢትዮጵያ ሕዝብ “በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ “የኤርትራን ሕዝብ የሰላምና የፍቅር መልካም ምኞት የማቀርበው በደስታ ነው”ሲሉ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።

በአማርኛ ንግግራቸውን የቀጠሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “እውን ስላደረጋችሁት ድል የተመላበት ታሪካዊ ለውጥ እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉ በአዳራሹ ለተሰበሰበው ሕዝብ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል።

በባህላችንና በታሪካዊ ጥልቅ ጥቅሞቻችን ላይ ለመንዛት የተሞከረውን ጥላቻና ትንኮሳ እንዲሁም ውድመት አሸንፈን ለልማት፣ብልጽግናና መረጋጋት በሁሉም መስክ አብረን መራመድና ወደፊት ለመገስገስ ቆርጠን ተነስተናል ብለዋል።

ይህንን ስምምነታችንንና ፍቅራችንን እንዲያውክ ለማንም አንፈቅድለትም ሲሉም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

“ማንም ፍቅራችንንና ስምምነታችንን ለመበተንና ለማወክ፣ርጋታችንና ሰላማችንን ለማሸበር ብሎም ለማጥቃት፣እድገታችንን ለማደናቀፍና ለማውደም እንዲፈታተነን አንፈቅድም” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም “በጋራ ጥረታችን የከሰርነውን አስመልሰን ለመጪው ጊዜ ግዙፍ ስራዎችን ሰርተን እንደምናሸንፍም እርግጠኞች ነን ሲሉ አጠንክረው ተናግረዋል።

“በድጋሚ ከባድ መስዋዕትነት ከፍላችሁ ያስመዘገባችሁትን ድል እያደነኩ ለዶክተር አብይ ብልህ አመራር ያለኝን ልባዊ ድጋፍና መልካም ምኞት እየገለጽኩ ድጋፌንም አጠናክሬ እንደምቀጥል በድጋሚ አረጋግጣለሁ” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ወደ ወደ አስመራ ከመመለሳቸው በፊትም የአዲስ አበባውን የኤርትራ ኤምባሲ በይፋ እንደገና መክፈታቸውም ታውቋል።

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ዛሬ አስመራ መግባታቸው ተሰምቷል።

የሁለቱን ሃገራት ሰላም ለማብሰር በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው የሙዚቃ ዝግጅት ሙሃሙድ አህመድ፣አሊ ቢራ፣ቴዲ አፍሮና አጫሉ ሁንዴሳን ጨምሮ በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።