ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ነገ ስልጣናቸውን ሊለቁ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 14/2011)የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በነገው ዕለት በይፋ ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ተገለጸ።

ላለፉት አምስት አመታት በስልጣን ላይ የቆዩትንና የስልጣን ዘመናቸው ሊጠናቀቅ አንድ አመት ሲቀረው ስልጣን የሚለቁትን ዶክተር ሙላቱ ተሾመን የሚተካ ፕሬዝዳንት በነገው እለት እንደሚሰየምም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።

ከመስከረም 27/2006 ጀምሮ ላለፉት 5 አመታት በፕሬዝዳንትነት የቆዩትን ዶክተር ሙላቱ ተሾመን የሚተካው ማን እንደሆነ በይፋ ባይታወቅም፣አንዳንድ ምንጮች የብአዴኑ ዶክተር አምባቸው መኮንን ፕሬዝዳንት ሆነው ሊሰየሙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የፕሬዝዳንትነቱን መንበር የተረከቡት ለ12 አመታት በፕሬዝዳንትነት ከቆዩት ከአቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ እንደነበርም ይታወሳል።

በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍል ተከትሎ በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው ቀውስ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከፓርቲው አመራርነት በፈቃዳቸው በመልቀቃቸው የስልጣን ዘመናቸው በአንድ የምርጫ ዘመን በመገደቡ አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ስልጣኑን የተረከቡት ከዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እንደነበር ይታወቃል።

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በስልጣን ላይ በቆዩበት 6 አመታት በሕግ የተሰጣቸውን ስልጣን እንኳን በአግባቡ እንዳይወጡ ይደረጉ የነበሩ ጫናዎችንም በመጽሃፋቸው ዘርዝረዋል።

ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ በግል ለፓርላማ በመወዳደራቸው ደሞዛቸውን ጨምሮ ጥቅማ ጥቅማቸው ሙሉ በሙሉ መቋረጡ ይታወሳል።

ላለፉት 14 ያህል አመታትም ይህንኑ መብት ተነፍገው ቆይተዋል።