ኢሳት (የካቲት 3 ፥ 2009)
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የሰባት ሃገራት ዜጎች ለተወሰነ ጊዜ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ያወጡት መመሪያ በሃገሪቱ የፌዴራል ይግባኝ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ውድቅ ተደረገ።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ በሲያትል ዋሽንግተ የተሰየመው የፌዴራል ፍርድ ቤት ፕሬዚደንቱ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ያወጡት አጨቃጫቂ መመሪያ የሃገሪቱን ህገመንግስት የሚጻረር ነው ሲል ሃሳቡ ውድቅ እንዲሆን ውሳኔ መሰጠቱ ይታወሳል።
ይሁንና የፕሬዚደንት ትራምፕ አስተዳደር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔን በመቃወም ጉዳዩን ይግባኝ ቢልም ይግባኙ የተመለከተ የፌዴራል ፍርዲ በት ይግባኙን ሃሙስ ውድቅ አድርጓል።
በካሊፎርኒያ ግዛት ሳንፍራንሲስኮ ከተማ የሚገኘው 9ኛው ተዘዋዋሪ የፌዴራል ችሎት በአሜሪካ የህግ ተቋምና መመሪያውን በሚቃወሙ የህግ አካላት ዘንድ የቀረበን የግራና ቀኝ ክርክር ከሁለት ቀን በፊት መስማቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሃሙስ ፌብሩዋሪ 9 የፕሬዚደንት ትራምፕን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ የታችኛውን ፍርድ ቤት አጽድቋል።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ሃሙስ ምሽት የተሰየሙ የይግባኙ ፍርድ ቤት ሶስት ዳኞች ያለምንም የሳብ ልዩነት የፌዴራሉ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ እንዲጸና መወሰናቸውን አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል።
በይግባኝ ፍርድ ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ ቅሬታ ያደረባቸው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የተላለልፈው ውሳኔ “ፖለቲካዊ ውሳኔ” በማለት በይግባኝ ውድቅ የተደረገው ጉዳይ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ለጋዜጠኞች ይፋ አድርገዋል።
ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚቀርበው አቤቱታቸውም ያለምንም ጥርጥር በድል የሚጠናቀቅ ነው ሲሉ ፕሬዚደንቱ አክለው አስታወቀዋል።
የፕሬዚደንቱ የጉዞ እገዳን በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው የነበሩት የዋሽንግተን እና የሚኔሶታ ግዛቶች የይግባኝ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን ደስታ እንደተሰማቸው ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም ሁለቱ ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ የህግ የበላይነት ያረጋገጠና አሜሪካንን በተገቢው መልኩ የገለጸ ነው ሲሉ ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛል።
የ90 ቀን የጉዞ እገዳን ተጥሎባቸው የነበሩ የኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ኤራን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና የመን ዜጎችም ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ውሳኔው ማረጋገጫ መስጠቱን የህግ አካላት አስረደተዋል።
የይግባኝ ፍርድ ቤቱ የፕሬዚደንት ትራምፕ አስተዳደር የጉዞ እገዳው የተጣለው ለብሄራዊ ደህንነት ነው ሲል ያቀረበው ሃሳብ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም ሲል በውሳኔው አፅንዖት መስጠቱን CNN ዘግቧል።
ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያመራል የተባለው ይኸው አነጋጋሪ ጉዳይ በበላይ ፍርድ ቤቱም በዳኞች መካከል ልዩነት ሊፈጥር እንደሚችል የህግ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የመረጧቸው አንድ ዳኛ ከቀናት በፊት ፕሬዚደንቱ በዳኞች ላይ በሚሰጧቸው አስተያየቶች ደስተኛ እንዳልሆኑ መናገራቸውንም መገናኛ ብዙሃን በመዘግብ ላይ ናቸው።