ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሰባት አገሮች ላይ የጣሉት የጉዞ እገዳ ተቃውሞ ገጠመው

ኢሳት (ጥር 22 ፥ 2009)

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሰባት ሃገራት ላይ የጣሉትን የጉዞ እገዳ ተከትሎ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።

ፕሬዚደንቱ ባለፈው አርብ ተግባራዊ ባደረጉት የውሳኔ ሃሳብ የኢራን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ሱዳን፣ ሊቢያ የመንና ሶማሊያ ዜጎች ለሶስት ወራት ያህል ጊዜ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ማድረጋቸው ይታወሳል። ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው ይኸው ውሳኔ አሜሪካ ያላትን የኢሚግሬሽን ፖሊሲ ማሻሻያ እስከምታደርግ ድረስ የሚዘልቅ እንደሆነ ተነግሯል።

ይሁንና ፕሬዚደንቱ ያስተላለፉት ውሳኔ በመቃወም አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፣ የህግ አካላት ፖለቲከኞችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የጉዞ እገዳው የአሜሪካ ህገ-መንግስት የሚጻረር ነው በማለት ተቃውሞን እያካሄዱ ይገኛል።

አዲሱ የጉዞ እገዳ በስራ ላይ ከዋለ በኋላ ወደ አሜሪካ ለመግባት በተለያዩ የአየር ማረፊያ ጣቢያዎች ደርሰው የነበሩ የኢራቅ፣ የኢራንና፣ ሌላ ሃገራት ዜጎች በየአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አሶሽዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።

በተለያዩ ዋና ዋና የአሜሪካ ከተሞች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የኒውዮርክ ከተማ ፍርድ ቤት በጆን ኦፍ ኬኔዲ አየር ማረፊያ እንዳይገቡ ተደርገው የነበሩ መንገደኞች በጊዜያዊነት እንዲለቀቁ ማድረጉም ተመልክቷል።

ይህንኑ የፍርድ ቤት ውሳኔ ተከትሎ በተለያዩ የአየር ማረፊያ ጣቢያዎች ታግተው የነበሩ መንገደኞች እንዲለቀቁ ቢደረግም ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉ መንገደኞች መኖራቸው የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የኒው ዮርክ ከተማ ባለስልጣናት እስከ እሁድ ድረስ ስድስት መንገደኞች መለቀቃቸውንና ሌሎች 10 ሰዎች በእገታ ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጣቸው CNN በዘገባው አመልክቷል።

ይሁንና ውሳኔው ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ምን ያህል የሰባቱ ሃገራት ዜጎች እንዳይገቡና እንዲመለሱ መደረጉን የተገለጸ ነገር የሌለ ሲሆነ፣ ከተለያዩ ሃገራት ወደ አሜሪካ ለመጓዝ የሞከሩ መንገደኞች አውሮፕላን እንዳይሳፈሩ መደረጉም ታውቋል።

ውሳኒያቸው ከፍተኛ ተቃውሞ የቀሰቀሰባቸው የአሜሪው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ውሳኔው ለቀጣዮቹ 90 ቀናቶች እንደሚቆይና ከእገዳው መነሳት በኋላ አሜሪካ የመግቢያ ቪዛ የመስጠት ሂደቷን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እንደምትጀምር ገልጸዋል።

የስደተኞች ሃገር የሆነችው አሜሪካ እንዲህ ያለ ውሳኔ በማስተላለፏ በጣም አሳፋሪና አሜሪካንን የማይገልጽ እንደሆነ የተለያዩ የአሜሪካ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።

የአሜሪካ ጦር ሰራዊት በኢራቅ የነበርው ተልዕኮ ለሰራዊቱ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ ኢራቃዊያን በተለየ ሁኔታ ወደ አሚሪካ እንዲገቡ ሲደረግ መቆየቱ ታውቋል።

በዚህ እድል ተጠቃሚ የሆኑ በርካታ ሰዎች ህጋዊ ሰነድ ይዘው ወደ አሜሪካ መግባት ቢሞክሩም በጉዞ እገዳው ሳቢያ ከሃገራቸው ጉዞ መጀመር እንዳልቻሉ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የካናዳ መንግስት በበኩሉ አሜሪካ በጣለችው የጉዞ እገዳ ሳቢያ በተለያዩ የአሜሪካ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች እንግልት የደረሰባቸውን ሰዎች በጊዜያዊነት ለመቀበል ፍላጎት እንዳለው እሁድ አስታውቋል።