ኢሳት (የካቲት 17 ፥ 2009)
የሱዳኑ ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር ግብፅ ለደቡብ ሱዳን መንግስት የተለያዩ ወታደራዊ የጦር መሳሪያዎችን እያቀረበች ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ገለጹ።
ግብፅ ለጎረቤት ደቡብ ሱዳን እያቀረበች ያለው ይኸው የጦር መሳሪያ የሱዳን መንግስት የስለላ መረጃዎች ተጠቅሞ ሊረጋገጥ መቻሉን ፕሬዚደንት አልበሽር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ይሁንና የሱዳኑ ፕሬዚደንት ግብፅ ለደቡብ ሱዳን መንግስት እያቀረበች ያለው የጦር መሳሪያ ለሃገራቸው መንግስት ስጋት እንደማይሆን አስታውቋል።
ከአንድ ወር በፊት የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚደንት ሳልባኪር ወደ ግብፅ በመጓዝ ከፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ማድረጋቸው መግለጹ ይታወሳል።
ሁለቱ ሃገሮች ግን በደረሱት ስምምነት ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ መገናኛ ብዙሃን የደቡብ ሱዳንና የግብፁ ፕሬዚደንት የአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀምን ጨምሮ በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ሲዘግቡ ቆይተዋል።
የሱዳንን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በደቡብ ሱዳን ያለው ግጭት እንዳይባባስ ለማድረግ ለየትኛውም ወገን የጦር መሳሪያ ላለማቅረብ ስምምነት እንዳለባቸው ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና ግብፅ ለሃገሪቱ እያቀረበች ነው በተባለው የጦር መሳሪያ ዙሪያ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት እስካሁን ድረስ የሰጡት ምላሽ የለም።
ከወራት በፊት የደቡብ ሱዳን መገኛኛ ብዙሃን የሳል-ባኪር መንግስት ከኢትዮጵያ የጦር መሳሪያዎች ለመግዛት ሚስጥራዊ ስምምነት እያደረገ እንደነበር በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረጉ የጽሁፉ መልዕክት (ደብዳቤ) ልወጦችን ዋቢ በማድረግ ዘግበዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተቃራኒው ኢትዮጵያ ለአማጺ ቡድን የጦር መሳሪያን ታቀርባለች በማለት ቅሬታን ሲያቀርቡ እንደነበርም የሚታወስ ነው።
ከተለያዩ ወገኖች እየቀረበ ያለውን ይህንኑ ቅሬታ ተከትሎም ኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግስት አንደኛው የሌላኛውን አማጺ ላለመደገፍና መጠለያ ላለመስጠት የሁለትዮሽ ስምምነት ማድረጋቸውም አይዘነጋም።