ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስ አዲስ አበባ ገቡ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 25/2010) ብጹእ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስ ከሩብ ክፍለ ዘመን ስደት በኋላ ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ።

ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስ እሁድ በሚሊኒየም አዳራሽም ከፍተኛ አቀባበል እንደተዘጋጀላቸውም ታውቋል።

ከሩብ ክፍለ ዘመን ስደት በኋላ ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስን የያዘው አይሮፕላን ዛሬ ከቀትር በኋላ 8 ሰአት ከ30 ደቂቃ ላይ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎለታል።

6ኛው ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች እንዲሁም የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች መሪዎች በአቀባበል ስነስርአቱ ላይ ተገኝተዋል።

ቀሳውስትና ዘማርያን የአቀባበል ስነስርአቱን ባስዋቡበት በዚህ ትዕይንት የፖሊስና የመከላከያ የእግረኛ ሙዚቃ ቡድን በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተገኝተው የአቀባበል ስነስርአቱን በሃገራዊ ሙዚቃ አድምቀዋል።

በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ ለፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስ አቀባበል ካደረጉ በኋላም የአቀባበሉን መንፈሳዊ ስነስርአት መርተዋል።

ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስን ይዘው አብረው አዲስ አበባ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የብጹእ ወቅዱስ ፓትሪያርኩ ወደ ሃገራቸው መመለስ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ደስታ ነው ሲሉ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልዩነቱ ግንብ መፍረሱን በቃል ካረጋገጠች በኋላ ዛሬ ይህንን በተግባር አሳይታለች ብለዋል።

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ የምንገነባውን ድልድይ የመጀመሪያውን ጡብ አስቀምጠዋል ሲሉም ተናግረዋል።