ፓሊሶች በአራት ኪሎ የሚገኙ ቤቶችን በእሳት አቃጠሉ

ጥር ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ለረጅም አመታት በአራት ኪሎ አካባቢ የኖሩ  ሰዎች ቦታው ለሼራተን ሆቴል ማስፋፊያ ይፈለጋል በሚል ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ሲነገራቸው እንደቆየ የተናገሩት አይን እማኞች፣ ነዋሪዎቹ በበኩላቸው መንግስት ተተኪ ቤት እስካልሰጣቸው ድረስ አካባቢውን ለቀው እንደማይሄዱ ሲከራከሩ ቆይተዋል። ዛሬ ጧት ወደ አካባቢው ያቀኑት ፖሊሶች ነዋሪዎቹ እቃዎቻቸውን ሳያወጡ በቤታቸው ላይ እሳት በመልቀቅ ቤታቸውን አቃጥለውባቸዋል። ነዋሪዎቹ በጩሀት ወደ ፓርላማ በመሄድ አቤት ቢሉም ሶስት ሰዎችን በመወከል ችግራቸውን እንዲያቀረቡ ተነግሮአቸዋል። ፖሊሶች ወደ አካባቢው በመድረስ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ነዋሪዎችን አባረዋቸዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የአይን ምስክር ለኢሳት እንደገለጡት፣ ተማሪዎች ደብተራቸውን እንኳን ሳያወጡ ቤታቸው እንደተቃጠለባቸው፣ ብዙዎችም በከፋ ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል።

በኢትጵያ ውስጥ በልማት ስም እየተበራከተ የመጣውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አለማቀፍ ሰብአዊ መብት ተማጓች ድርጅቶች ችላ እንዳሉት ተመልክቷል። በአላማጣ ላለፉት አንድ ወራት የከተማው ህዝብ በልዩ ፖሊሶች ሲዋከብ እንደነበርመዘገባችን ይታወሳል። በአዲስ አበባ ላፍቶ ክፍለከተማ ቤታቸው የፈረሰባቸው በርካታ ነዋሪዎች አሁንም በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸው ይታወቃል።