ፒተር ሀይንላይን ወገቡ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ተዘገበ

ግንቦት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባለፈው አርብ ከፒተር ሀይንላይን ጋር  ለአንድ ቀን ከታሰረች በሁዋላ የተለቀቀችውና የቪኦኤው ዘጋቢ አስተርጓሚ የሆነችው ጋዜጠኛ  ስመኝሽ የቆዬ እንደገለጸችው፤ዓርብ ዕለት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ገደማ አወሊያ ትምህርት ቤት ቆይተው ሲመለሱ ሲቪል የለበሱ የደኅንነት ሰዎች በፖሊስ ካስቆሟቸው በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄድ እንዳለባቸው ይገልጹላቸዋል:: ጋዜጠኛ ሄይንላየንና ስመኝሽም፣ ‹‹ምን እንዳደረግን ሳናውቅ አንሄድም›› የሚል ምላሽ ይሰጣሉ::

ሪፖርተር እንዳለው ፦”ትሄዳላችሁ አንሄድም” የሚል ክርክር ለሁለት ሰዓት ያህል ሲያካሂዱ ከቆዩ በኋላ ፖሊሶቹ በኃይል በመጠቀም ጋዜጠኞቹን ወደ ተለያዩ መኪኖች እንዲገቡ አድርገዋቸዋል።

በስተመጨረሻም  የፖሊሶቹን ትዕዛዝ ተቀብላ ወደተዘጋጀላት መኪና መግባቷን የጠቀሰችው  ጋዜጠኛ ስመኝሽ፤ ሄይንላየን ግን ፖሊሶች በኃይል ተሸክመው ፒክአፕ መኪና ውስጥ ሊያስገቡት ሲሞክሩ ‹‹አልገባም›› ብሎ ሲታገል በመውደቁ ወገቡ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግራለች።

ስመኝሽ እንደምትለው፣ ፖሊሶች ወደ ኮልፌ ፖሊስ ጣቢያ ይዘዋቸው የሄዱት ሄንላየንን እየጐተቱ መኪና ውስጥ ካስገቡት በሁዋላ ነው።

የዓለማቀፍ የፕሬስ ተቋማት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፤ጋዜጠኞችን በማዋከብ፣ በማሰቃዬት፣ ሙያዊ ነፃነታቸውን በአሳሪ ህጎች በመንፈግ፣በማሳደድ እና በፈጠራ ክስ በማሰር  ኢትዮጵያ ከዓለማችን በግንባር ቀደምነት የምትጠቀስ  አስፈሪ አገር ሆናለች።

የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ ሽመልስ ከማል ሄይንላይን የታሰረው ፖሊሶች መታወቂያ እንዲያሳይ እና ስለማንነቱ እንዲገልጽላቸው ሲጠይቁት ፈቃደኛ ባለመሆኑ  ምክንያት ነው በማለት  ባለፈው ቅዳሜ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ መናገራቸው ይታወሳል።ስለዚህም ፖሊሶቹ ጋዜጠኛ መሆኑን ባለማወቃቸው ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዱት ነበር አቶ ሽመልስ የተናገሩት።

ከፒተር ሀይንላይን ጋር አብራ ታስራ የተፈታችው ጋዜጠኛ ስመኝሽ ስለሁኔታው የሰጠችው ገለፃ ግን  አቶ ሽመልስ የተናገሩት ከ እውነት የራቀ መሆኑን ነው የሚያመለክተው።

ጋዜጠኛ ስመኝሽ እንዳለችው፤  እሷ እና ሀይንላይን በፖሊሶች በሀይል የታሰሩት ወደ አወሊያ ገብታችሁ ዘገባ መሥራት አትችሉም ተብለው እንጂ፤መታወቂያ እንዲያሳዩ አለያም ስለማንነታቸው እንዲገክጹ ተጠይቀው እምቢተኛ ስለሆኑ አይደለም።

የአቶ መለስ  መንግስት የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በኢትዮጵያ እንዳይደመጥ በማድረጉ ምክንያት ተቃውሞ ሲቀርብበት ፤አቶ ሽመልስ   ተቃውሞው ስህተት እንደሆነ የተናገሩት ፦መንግስታቸው ራዲዮ ጣቢያን ጃም ለማድረግ ዲሞክራሲያዊ ባህርይው እንደማይፈቅድለት በማስረዳት ነበር።

ይሁንና አቶ ሽመልስ ይህን ባሉ ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአደባባይ፦”ጃም ያደረግነው እኛ ነን”ማለታቸው ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide