ጥቅምት ፲፫ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ በዛሬው እለት ዳግም ለአንባቢያን መቅረቧን የጋዜጣው አዘጋጅ ለኢሳት ሬድዮ አስታወቀ።
ዳግም ለሕትመት በቅታ ዛሬ ለአንባቢያን የተሰራጨችው ፍኖተ-ነጻነት ጋዜጣ፤ በግል ማተሚያ ቤት መታተሟንም የጋዜጣው አዘጋጅ ብስራት ወልደሚካኤል ለኢሳት ገልጿል።
የግል ማተሚያ ቤቱ ፍኖተ ነጻነትን በመደበኛ የጋዜጣዋ የቀድሞ መጠንና ቅርጽ ለማውጣት የወረቀት ችግር አለበት ያለው ጋዜጠኛ ብስራት፤ በዚህ ምክንያትም በኤ ፎር (A᎓ 4) መጠን አጠርና ስብስብ ብላ ወጥታለች ብሏል።
ከብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋር ያለው ችግር እስካሁንም አለመፈታቱን የጋዜጣዋ አዘጋጅ ያስታወቀ ሲሆን፤ በግል ማተሚያ ቤት ጋዜጣዋን በማሳተም በቅርጽ እንጂ በይዘት ሳትለወጥ ህትመቱ ይቀጥላል ብሏል።
ጋዜጠኛ ብስራት ወ/ሚካኤል የጋዜጣዋ ቅርጽ መለወጥ በአንባቢያን ዘንድ የተለየ አቀባበል አለማስከተሉን ገልጾ እንዲያውም ጋዜጣው ዛሬ ለገበያ ቀርቦ ከዋጋ በላይ በመሸጥ እንደሚገኝ አስታውቆ፤ ህዝቡ ጋዜጣዋን ለማግኘት እየተረባረበ እንደሆነ ገልጿል።