ነኅሴ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከምርጫው ማግስት ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በፖሊስ ተይዘው ነሃሴ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. እያንዳንዳቸው በ15 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ተጠይቀው የነበሩት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ፣ ዋስትናቸው በአቃቤ ህግና በፖሊስ መታገዱን የፓርቲው የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ በአመራሮቹ ላይ ላቀረበው ክስ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ነሃሴ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምርጫው ማግስት እየታደኑ የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ 8 የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን እያንዳንዳቸው የ15 ሺህ ብር ዋስ አቅርበው እንዲፈቱ የወሰነ ሲሆን ሁለቱ ወዲያውኑ ወጥተዋል፡፡
ይሁንና የዋስትናው ገንዘብ እስኪሞላላቸው እስር ቤት የቆዩት 6ቱ አመራሮች ማለትም ልዑልሰገድ እምባቆም ፣ ፋንታሁን ብዙአየሁ፣ መንግስቴ ታዴ፣ አዳነ አለሙ፣ መምህር ስማቸው ምንይችልና አበባው አያሌው ትናንት ነሃሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የክልሉ አቃቤ ህግና ፖሊስ ለማረሚያ ቤቱ ባቀረቡት ጥያቄ ዋስትናቸው መታገዱ ታውቋል፡፡ አመራሮቹና አባላቱ ዋስትናቸው የታገደው ገንዘቡን ካስያዙ በኋላ መሆኑንም ነገረ -ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡