ኢሳት (የካቲት 18 ፥2008)
በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እንዲፈቱና በሃገሪቱ ያለን ጭቆና እንዲቆም የሚጠይቅ ተቃውሞ አርብ ፍል ውሃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ተውፊቅ መስጊድ ተካሄደ።
የአርብ ልዩ የጾም (ጁምዓ) ስነ-ስርዓት ተከትሎ በተካሄደው በዚሁ ተቃውሞ የሙስሊም ማህበረሰብ መፈክሮች የተጻፉባቸው ፊኛዎችን ወደሰማይ መልቀቃቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በድምፅና ድምፅ አልባ የሆኑ ተቃውሞዎች በአንዋር መስጊድ መካሄዳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ተቃውሞ ወደሌላ መስጊድ ሲዛመት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ተነግሯል።
“ብሄራዊ ጭቆናን እንታገላለን፣ ኮሚቴው ይፈታ፣ ጭቆናው ይብቃ” እንዲሁም “ድምጻችን ይሰማ” የሚሉ መፈክሮች በፊኛዎቹ ላይ ከተጻፉት መካከል የሚገኙበት እንደሆነም ታውቋል።
የሙስሊሙ ማህበረሰብ መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል በማለት ተቃውሞአቸውን ከሶስት አመት በፊት ጀምሮ በማካሄድ ላይ መሆናቸው ይታወሳል።
በሙስሊሙ ማህበረሰብ የተወከሉ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎም ለተቃውሞ በተለያዩ ስልቶች መቀጠሉን የሰልፉ አስተባባሪ የሆነው ድምጻችን ይሰማ ይገልጻል።
የፍትህ ሚኒስቴር ለእስር ተዳረገው የእስር ቅጣት ከተላለፈባቸው ከ20 አባላት መካከል አምስቱን በምህረት መልቀቁ የሚታወስ ሲሆን የሙስሊም ማህበረሰብ ያለምንም ወንጀል የታሰሩት ቀሪዎች አባላትም እንዲለቀቁ በመጠየቅ ላይ ናቸው።