ፊሊፕ ሃሞንድ ስለ አቶ አንዳርጋቸው መጠየቅ አለባቸው ተባለ

ግንቦት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-  የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፊሊፕ ሃሞንድ ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝታቸው ከየመን ታፍነው የተወሰዱትን የሶስት ልጆች አባትና የዴሞክራሲ አቀንቃኝ የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱ ጥያቄ እንዲያቀርቡ የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ የሚከታተለው ሪፕሪቭ የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ጥያቄ አቅርቧል።

አቶ አንዳርጋቸው ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ በሞት ፍርድ የሚያስቀጣ ወንጀል ተከሰው በኢትዮጵያ ወህኒ ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ሪፕሪቭ አስታውሶ ፣ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ተለቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው ይመለሱ ብሎአል።  በኢትዮጵያ አሰቃቂ እስር ቤቶች ውስጥ ሰቆቃ ሳይፈጸምባቸው እንደማይቀር ሪፕሪቭ  ገልጾ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውም  ይህን ያጠናክራል ብሏል።

የአቶ አንዳርጋቸው ልጅ የሆነችው ታዳጊ ምናቤ   የእንግሊዝ መንግስት አባቱዋ እንዲፈታ ምንም እርምጃ አልወሰደም በማለት በውጭ ጉዳይ ባለስልጣናት ላይ ክስ መክፈቷ ይታወሳል። የሞት ፍርድ ተቃዋሚ  የሪፕሪቭ በእንግሊዝና አሜሪካ ዋና ዳሬክተር የሆኑት ማያ ፎ እንዳሉት ”አቶ አንዳርጋቸው ታፍነው ነው ወደ ሞት ፍርድ ነው የተወሰዱት። ይህም የኢትዮጵያ መንግስትን ሕገወጥነት ማሳያ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ ፊሊፕ ሃሞንድ አቶ አንዳርጋቸው ከታሰሩበት ተፈተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ አለባቸው።” ሲሉ በአጽኖት ተናግረዋል።