ጥር 8 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው ፍኖተ ነጻነት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውጥረት ሰፍኖ መሰንበቱን አስነብቧል።
በምእራብ ጎጃም ዞን በአዴት ከተማ ቤት ከማፍረስ ጋር በተያያዘ ተቃውሞ አንድ የወረዳ ባለስልጣን መገደሉንና ሎሎች ሶስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጧል። በአሁኑ ጊዜም ህዝቡ ቤቱን ላለማስፈረስ በመወሰኑ፣ በአካባቢው ውጥረት መስፈኑን ጋዜጣው ዘግቧል።
በጅማ ዩኒቨርስቲ ደግሞ አንድ የግቢው ሰራተኛ የተወሰኑ ተማሪዎችን ሰብስቦ እናንተ የብርሀኑ ነጋን ፖለቲካ ታራምዳላችሁ ብሎ ለማስፈራራት መሞከሩን ተከትሎ፣ ተማሪዎቹ አንተ ማነን? ለምን ትከፋፍለናለህ የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳታቸው ውጥረት ተፈጥሮ ነበር።
የሸዋና የጅማ አዋሳኝ በሆነው በጊቤ በረሀም እንዲሁ ከ20 አመት በፊት ከሸዋ፣ ከጎጃምና ከወሎ የሄዱ 2 መቶ የሚሆኑ አባዎራዎች ካለሙት መሬታቸው እንዲፈናቀሉ በመደረጋቸው ለልመና ተዳርገዋል።
በደሴ ዩኒቨርስቲ ደግሞ አንድ የፖለቲካ አቀንቃኝ የነበረ ተማሪ ተገድሎ በመገኘቱ ተማሪዎች ትምህርት አቁመው ሰልፍ ሲወጡ በፌደራል ፖሊስ እንዲበተኑ ተድርጓል።
በአዳማ ዩኒቨርስቲ ከብሄር ጋር በተፈጠረ ግጭት የታሰሩ ተማሪዎች አሁንም አልተፈቱም። በወለጋ ዩኒቨርስቲም እንዲሁ ከአንድ ተማሪ መመረዝ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ውጥረት እንዳለ ነው።
ጋዜጣው በጋምቤላና በደቡብ ክልሎች የተከሰቱትን በርካታ ችግሮችንም ዘርዝሮ አቅርቧል።