ጥር ፲፪ ( አሥራ ሁለት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በብአዴን አንጋፋ አባሉ አቶ ዓሊ ሱሌይማን የሚመራው የፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን የባለሥልጣናትን ሐብት መመዝገብ ከጀመረ ሰባት ዓመታት ቢያስቆጥርም እስካሁን የምዝገባ መረጃውን ለህዝብ እና ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑ እያነጋገረ ነው፡፡
በሀገር ውስጥ ከሚገኙ መገናኛ ብዙሃን አንዳንዶቹ በስም በመጥቀስ የባለስልጣናቱ የሐብት ምዝገባ መረጃ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ ኮምሽኑ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን ታውቋል፡፡
በሐብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት ኮሚሽኑ ከህዳር ወር 2003 ጀምሮ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እና ሌሎች በተዋረድ ያሉ ባለስልጣናት ሐብት በይፋ መመዝገብ የጀመረ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ሁለት ኣመታት ብቻ 2934 ተሿሚዎች፣ 628 የህዝብ ተመራጮች፣46 ሺ 639 የመንግሥት ሠራተኞች በአጠቃላይ 50 ሺ 201 ዋና ዋና የሚባሉ ባለስልጣናትን ሐብት መዝግቧል፡፡ ኮምሽኑ ሐብቱን መመዝገብ ብቻም ሳይሆን መረጃዎቹን አሰናድቶ አስቀምጧል።
የኮምሽኑ ምንጫችን እንደሚለው የሐብት ማሳወቅና ምዝገባ ጠቀሜታዎች አንዱ የሙስና ወንጀል ምርመራን ለማቀላጠፍ የሚረዳ የመረጃ ግብኣት ሆኖ ማገልገል መሆኑን ጠቅሶ ፣ ይህ ካልተሟላ ግን መመዝገቡ ብቻውን ለፕሮፓጋንዳ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ የለውም ብሎአል፡፡
ኮምሽኑ መረጃዎን ለህዝብ ይፋ ያላደረገው ይህን የሚመለከት ራሱን የቻለ ድረገጽ እያሰራሁኝ ስለሆነ ነው በሚል በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠቱን፣ ይህ ስራ ግን ከተጠናቀቀም በሃላ በአስፈጻሚው አካል ጣልቃ ገብነት የምዝገባ መረጃዎቹ ይፋ መሆን እንዳልቻሉ ምንጫችን ጠቁሟል፡፡
ከሳምንት በፊት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሙስናና ብልሹ አሰራሮች የሚጠረጠሩ ከፍተኛ የአመራር አካላትን መክሰስ ያልተቻለው ማስረጃ ባለመኖሩ መሆኑን በመጥቀስ የጸረ ሙስናን ሐብት ምዝገባ መረጃ ጭምር በመጠቀም ያለአግባብ ሐብት ያፈሩ አመራሮችን ለህግ ለማቅረብ የህዝቡን ድጋፍ ጠይቀው ነበር።