ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚያወጣ መሬት ማስመለሱን ገለጸ

ሐምሌ ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኮሚሽኑ ባለፉት 5 አመታት ፣ 5 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የተዘረፈ መሬት ማስመለሱን ገልጿል። 27 የመኖሪያና የንግድ ቤቶችንና 22 መኪኖችን ማስመለሱንም ገልጿል።
ኮሚሽኑ ሙስናን ለመዋጋት ጥረት ቢደረገም ሙስና አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አስታውቋል። 90 ሺ የመንግስት ባለስልጣናት ሃብታቸውን ማስመዝገባቸውን ኮሚሽኑ ቢገልጽም፣ መቼ ይፋ እንደሚያደርግ ወይም እስካሁን ይፋ ለማድረግ ለምን እንዳልቻለ የገለጸው ነገር የለም።
ከሙስና ጋር በተያያዘ 5 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ መሬት መዘረፉ በመንግስት ደረጃ ከተገለጸ፣ መንግስት ያልገለጸው እጅግ ከፍተኛ የሆነ የመሬት ሃብት በሙስና መዘረፉን መገመት ይቻላል የሚለው ዘጋቢያችን፣ ዜናው በአገራችን ያለውን ሙስና ፣ የዜጎችን ከመሬታቸው መፈናቀልና በአገሪቱ ስር የሰደደውን የቤት ችግር መንስኤ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ሲል አስተያየቱን አስፍሯል።