ጥንታዊው የገዳ ስርዓት በዩኔስኮ ቅርስነት ተመዘገበ

ኅዳር ፳፩ (ሃያ አንድ)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :-የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ተቋም ዩኔስኮ በመዲናችን አዲስ አበባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኤኮኖሚክስ አዳራሽ ባደረገው 11ኛው መደበኛ ስብሰባው ላይ ጥንታዊውን የገዳ ስርዓትን በዓለም በማይዳሰሱ ቅርስነት መዘግቦታል።

የገዳ ስርዓት በኢትዮጵያ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት ዘንድ ባሕላዊ አስተዳደራዊ ስርዓት ሆኖ  ለዘመናት እውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር ያገለገለ ጥንታዊ አስተዳደራዊ መዋቅር መሆኑ ለቅርስነት እንዳስመረጠው ዩኔስኮ ገልጿል። የገዳ ስርዓት በማኅበረሰቡ ውስጥ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና የግጭት ማስወገጃ ስርዓቶችን ያቀፈ እና በተጨማሪም የሴቶችን ሰብዓዊ መብት በማስከበር ረገድም ከፍተኛውን ሚና መጫወቱን ተሰብሳቢዎቹ አውስተዋል።

የገዳ ስርዓት የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት ሞራላዊ እሴቶች ተጠብቀው ከትውልድ ትውልድ እንዲተላላፉ እና ባሕላዊ መስተጋብሮች እንዳይጠፉ ዓይነተኛ አስተዋጾ አድርጓል። የገዳ አስተዳደር አምስት ደረጃዎች ያሉትና በአንድ አባገዳ የሚመራ ሲሆን፣  በየስምንት ዓመቱም በዴሞክራሲያዊ ባህላዊ አሰራር አዲስ መሪ አባገዳ ይሰየማል። በገዳ አስተዳዳሪነት የተመረጡ አባገዳዎችና በእርከን የተሾሙ የአገር ሽማግሌዎች በኦዳ ዛፍ ጥላ ስር በመሰባሰብ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ። የሕብረተሰቡን ባህልና ትፊቶች የመጠበቅ ግዴታዎች ይወጣሉ።

ከኢትዮጵያው ገዳ አስተዳደር በተጨማሪ  ኡጋንዳ፣ ኩባ፣ ዩክሬን፣ ካንቦዲያ፣ ባንግላዲሽ፣ የግብጽ፣ ዶሜኒካ ሪፐብሊክ፣ ፖርቱጋል፣ ቤልጅየም እና ቻይና የተለያዩ እሴቶቻቸውን በማይዳሰሱ ቅርስነት እንደተመዘገበላቸው ዩኔስኮ ዘግቧል።