ጥር ፲፩ (አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ አስታወቀ

በአውሮፓዊያን ዘመን አቆጣጠር በ2015 ቁጥራቸው ከ100 ሽህ በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያዊያንና የሶማሊያ ስደተኞች ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በጀልባ የመን ገብተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑት አድሪያን ኤዲዋርድስ ” ስደተኞቹ ወደ የመን የሚያደርጉት የባሕር ጉዞዋቸውና የመን ውስጥ ከገቡ በኋላ የሚጠብቁዋቸው ሁኔታዎች በጣም አደገኛ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት 36 የሚሆኑ ስደተኞች በጀልባ ሲጓዙ ሰምጠዋል” ሲሉ ስደተኞቹ ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን አስታውቀዋል። ወደ የመን ካቀኑት ስደተኞች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ወይም 82 ሽህ 268ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
በየመን በሳኡዲ በሚመራው የዓየር ጥቃት ሳቢያ 6 ሽህ የሚሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውንና በጦርነቱ ምክንያት 2.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የመናዊያን ከትውልድ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ሚድል ኢስት አይ አክሎ ዘግቧል። ከእነዚህ ሟቾች መካከል ምን ያክሉ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ በዘገባው አልተጠቀሰም።
በሌላ ዜና ደግሞ በሶማሊላንድ ራስ ገዝ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 300 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው ለመላክ ዝግጅታቸውንን ማጠናቀቃቸውን የሶማሊላንድ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የሶማሊላንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር የሆኑት አሊ ዋራን አዴ ”ሁሉም ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ ነው የሚኖሩት። በሚቀጥለው ወራት ሁሉንም ወደ አገራቸው ለመላክ ዝግጅታችንን አጠናቀናል” ማለታቸውን ሆርስ ሚዲያ ዘግቧል።አብዛኞቹ የሚመለሱት የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሶማሊላንድ መንግስት በጅምላ “ሕገወጥ ስደተኞች” በማለት ኢትዮጵዊያንን ስደተኞችን አስሮ ካለፍላጎታቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያደርገውን ሕገወጥ ድርጊት እንዲያቆም እየጠየቁ ናቸው።
ሶማሊላንድ እስካሁን አለማቀፍ አውቅና አላገኘችም። በርካታ ዜጎቿ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩባት ሶማሊላንድ፣ በኢህአዴግ መንግስት ግፊት ስደተኞችን ከአገሯ ለማስወጣት የጀመረችው አዲስ እንቅስቃሴ ለወደፊቱ አገሪቱን የሚጎዳ መሆኑን ታዛቢች ያስጠነቅቃሉ።