ሐምሌ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፍትህ ሚኒስቴር በሽብረተኝነት ክስ ለሚከሰሱ ጋዜጠኞችና የሃይማኖት መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና አባላት ጠበቃ በመሆን የሚታወቁትን አቶ ተማም አባ ቡልጉን የዲሲፒሊን ግደፈት ፈጽመዋል በሚል ለአንድ አመት ከ7 ወር አግዷቸዋል። መታገዳቸውን ከሚዲያ የሰሙ ጓደኞቻቸው እንደነገሩዋቸው የገለጹት አቶ ተማም፣ በህጉ ቢሆን ነሮ የእግድ ደብዳቤው ከሚዲያ በፊት ለእርሳቸው መድረስ ይገባው እንደነበር ተናግረዋል። ድርጊቱ እርሳቸውን በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ታስቦ የተወሰደ ነው የሚሉት አቶ ተማም፣ ምንም አይነት የስነ ልቦና ጫና እንደማይፈጥርባቸውም ገልጸዋል።
የእርሳቸው የእግድ እርምጃ በሽብረተኝነት ወንጀል ከተከሰሱት ከእነ አቶ አቡበክር እና ከነዘላለም ወርቃለማሁ ጉዳይ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል የገለጹት አቶ ተማም፣ እስካሁን ሲያደርጉት የነበረው፣ ማድረግ ካለባቸው እጅግ ጥቂቱን መሆኑን ተናግረዋል። በገዛ አገሬ የሆኑ ሰዎች የመስራት መብቴን በማገዳቸው መቼውንም የማልረሳውና ይቅርታ የማላደርግለት ነገር ነው ሲሉ ጠበቃው አክለው ገልጸዋል።
ከአቶ ተማም አባ ቡልጉ ጋር የተደረገው ቃለመልልስ ከመጨረሻ ዜና ቀጥሎ እንደሚቀርብ ለመግለጽ እንወዳለን።