ጠቅላይ ሚንስትሩ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ያደረጉት ውይይት በጎ ጅምር ቢሆንም አፋኝ ሕጎችን በማንሳት የፖለቲካ ምህዳሩ ሊሰፋ ይገባል ተባለ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 05 ቀን 2010 ዓ/ም) ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ከበዓለ-ሲመታቸው ጀምሮ ያሰሙት ንግግር ለአገራችን ፖለቲካዊ መረጋጋት ተስፋ ሰጪዎች ቢሆንም ሁሉንአቀፍ ለውጥ ለማምጣት አፋኝ ሕጎችን በማንሳት ተግባራዊ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞች ተናገሩ።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ከተመረጡበት ጊዜ ጀምሮ የሕዝብ ግንኙነታቸውን በስፋት መቀጠላቸው ባለድርሻ አካላትን ተቃዋሚዎቹን ማነጋገራቸው መልካም ቢሆንም ከተለመደው የተለየ አይደለም። ከዚህ በፊት ተደርገው የነበሩትን ድርድሮች ትርጉም ሰጥተው ድርድሩ እንዲቀጥል መናገራቸው፣ የአገር አቀፍ ፓርቲዎችን ብቻ ጠርተው አነጋግረዋል። ታዋቂ ግለሰቦችና፣ ፖለቲከኞች በግብዣው ላይ ሲታደሙ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አለመገኘታቸው ተገቢ አለመሆኑን የኦሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ሊ/መንበር የሆኑት አቶ ግርማ በቀለ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በብሄራዊ ቤተመንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የእራት ግብዣ በማድረግ መወያየታቸውና ተቃዋሚዎችን የሚለውን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተብሎ መነሳቱ መልካም ጅምር ነው። ሆኖም ግን ሰፊ ድርድርና ውይይት ያስፈልጋል።
ለዚህ ሁሉ ቁልፍ የሚሆነው አፋኝ ቀፍዳጅ የሚባሉ ህጎችን በማንሳት የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት ያስፈልጋል። ይህ ጅምር መነሻ ነው። የግል ፕረሱ ቢያንስ ከ1997 ዓ.ም በፊት እንደነበረው መመለስ አለበት። በአሁኑ ሰዓት ይህ ነው የሚባል የፕሬስ ውጤት የለም። ጋዜጠኞች ሳንሱር ቀርቶ ሳይሳቀቁ በሚዛናዊነት የሚሰሩበት ሁኔታ ሊመቻችላቸው ይገባል። ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚንስትሩ ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል ሲል ጋዜጠኛ ነብዩ ገልጿል።