(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17/2011) አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ነች ሲሉ የኦዲፒ ሊቀ መንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) 29ኛ የምስረታ በዓል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሲካሄድ ዶክተር አብይ እንደገለጹት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ሀዋሳ፣ ጅማ፣ ነቀምት ሄዶ እንደሚሰራውና የኔ ናቸው እንደሚለው ሁሉ አዲስ አበባም የሁሉም ኢትዮጵያውያን መኖሪያ መሆኗን ማወቅ ያስፈለጋል።
በኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) 29ኛ የምስረታ በዓል በመድረክ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኦዴፓ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፥ የኦዴፓን የምስረታ በዓል ስናከብር ለአዳዲስ ድል እና ገድል እየተዘጋጀን መሆን አለበት ብለዋል።
ኦዴፓ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚኮራባት፣ የሚሰራባትና የማይሸማቀቁበት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በቁርጠኝነት ይሰራልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከራሷ ዜጎች በዘለለ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የምትበቃ በመሆኗ ይህንን ከግምት ማስገባት መልካም ነው ሲሉም ገልፀዋል።
የኦዴፓ አላማ ኢትዮጵያውያን በእኩል ድምጽ በነጻነት የሚኖሩባትን ሀገር መፍጠር ነው፤ በዚህ ረገድም ከሁሉም ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክትም መለያየትን የሚሰብኩ አስተያየቶችን ወደ ጎን በመተው በጋራ መቆም አለብን ሲሉም ገልጸዋል።
ለኦዴፓ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ፥ ኦዴፓ በማንኛውም ሁኔታ ድምፆች መታፈን የለባቸውም የሚለውን አላማ ይዞ መነሳቱ መዘንጋት የለበትም ብለዋል።
ማንኛውም ሀሳብ የሚንሸራሸርበት ኢትዮጵያን መፍጠር የትግላችን ውጤት መሆኑንም ማወቅ አለብን ነው ያሉት።
አሁን ካለንበት የለውጥ ሂደት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስደንጋጭ ሀሳቦችን ልትሰሙ ትችላላችሁ፤ እነዚህን ከመደናገጥ ይልቅ የተሻለውን ሀሳብ በመውሰድ ሌላውን ወደጎን መጣል አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን የጀመርነውን ድል ማንም ወደ ኋላ አይመልሰውም ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለእህት ድርጅቶች ባስተላለፉት መልክትም በተጠናከረ እና በወንድማማችነት መንፈስ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ እናሸጋግር ብለዋል።
በዚህ በዓል ላይ የተገኙት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ሊቀመንበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ለውጥ ሁሉ ፈተና እንዳለው ገልጸው ፈተናውን በጋራ በመሰለፍ መወጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለመስራት ሁሉም መነሳት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።