ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በ35ኛው የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌስቲቫል ላይ እንዲገኙ የቀረበው ጥያቄ በማህበሩ በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ ተገለጸ።
(ኢሳት ዜና ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ/ም) ዶክተር አብይ አህመድ በዳላሱ ዝግጅት ላይ እንዲገኙ ጥያቄ የቀረበው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በቁጥር ዋሸ 09-620-2010 በጻፈው ደብዳቤ አማካይነት ነው።የማህበሩ አመራሮች ይህን ጥያቄ ተከትሎ ባሰባሰቡት ድምጽ 65 በመቶ ያህሉ ድምጽ ሰጭ እንዲገኙ ፍላጎቱን የገለጸ ቢሆንም፣ አንዳንድ ወሳኝ ጉዳዩችን በማጤን በራሳቸው ውሳኔ ለማሳለፍ መገደዳቸውን ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ በሰጡት ድምጽ በተቀራራቢ ውጤት በዘንድሮው ዝግጅት መገኘት የለባቸውም የሚለው አሸናፊ ሆኗል።ማህበሩ ውሳኔውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የዶክተር አብይ አህመድን ጥያቄ በአክብሮት እንደተቀበለው ሆኖም፣ ጥያቄው የቀረበው ዝግጅቱ ሊጀመር ጥቂት ቀናት ሲቀረው ከመሆኑ አኳያ በስቴዲየም ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ጭንቅንቅ ታሳቢ በማድረግ ፣ለታዳሚው ህዝብ ደህንነት የሚፈጸመውን ክፍያ ፌዴሬሽኑ ከፍሎ ያጠናቀቀ በመሆኑ ጥያቄውን ለመቀበል እንደተቸገረ ገልጿል።
አክሎም ወደፊት በሚደረጉ ዝግጅቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጋበዙበትን መንገድ እንደሚያጤነው አስታውቋል።
ዶክተር አብይ መጋበዝ አለባቸው ብለው ድምጽ የሰጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በማህበሩ ውሳኔ ላይ ተቃውሞ ሲሰነዝሩ የዋሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በውሳኔው ቅር ብንሰኝም በዲሞክራሲ እንደሚያምን ዜጋ የማህበሩን ውሳኔ አክብሮ ከመቀበል ውጭ ውዝግብ ውስጥ መግባት አያስፈልግም ብለዋል።