ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሚፈሰው የንጹሀን ደም በአስቸኳይ እጃቸውን ያነጹ ዘንድ ተጠየቁ

ነሃሴ  ( ሃያ ስድስ ) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :- ይህን የጠየቁት  ታዋቂው ወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ነው

“ከጌታ ምሕረትን ተቀብዬ ላለፉት 27 ዓመታት ዘር፣ ጎሣ፣ ቀለም፣ ጾታ፣ እምነትና የፖለቲካ አመለካከት ሳልለይ ለትንሽ ለትልቁ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ስሰብክ የኖርኩ ነኝ” ያሉት ወንጌላዊ ያሬድ፣

ዛሬ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍሎት በልብ ጭንቀትና በብዙ ዕንባ ነው።› በማለት ነው ደብዳቤያቸውን የጀመሩት፥

“የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል በዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ የሚፈቅደውን ንግግርዎን አድምጫለሁ።” ያሉት ወንጌላዊ ያሬድ፤

ከተቀመጡበት ወንበር ግዝፈትና ከከበበዎት ውጥረት አንጻር የገቡበትን አስጨናቂ ሁኔታ ፣ እንዲሁም ውሳኔው የጋራ እንጂ የግልዎ ብቻ እንዳልሆነ ብረዳም  በአንደበትዎ የተነገረውና በታሪክ መዝገብ ተቀርጾ

የሚኖረው ይህ ውሳኔዎ በእግዚአብሔር፣ በሰውና በኅሊናዎ ዘንድ ከፍተኛ ተጠያቂነት እንደሚያመጣብዎ ሳስብ ከልብ አዝናለሁ።” ብለዋል፤

ወንጌላዊ ያሬድ አክለውም “ እርሶ በእግዚአብሔር ምህረት የተፈጠሩ፣ በምሕረቱ ያደጉና አሁን ለደረሱበት ከፍተኛ የኃላፊነት ሥፍራ የበቁ መሆንዎን በሚገባ ያውቃሉ። ይህን ለእርስዎ የተሰጥዎትን የመኖር መብት ለሌሎች

ይነፍጋሉ ብዬ አላስብም። ሆኖም አሁን በእርሶ መሪነት በገዛ አንደበትዎ የተሰጠው ይህ ውሳኔ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምትክ የማይኖራቸው ኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ ሞት የሚያጠላ ነው።” ብለዋል።

“ይህ ዛሬ ድምጹን ለማሰማት በየሥፍራው እንደ አሸን የፈላው ሕዝብ ላለፉት 25 ዓመታት ለኢሕአዴግ አመራር ጸጥ ለጥ ብሎ የተገዛ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ባረፉ ጊዜ ዕንባውን የረጨ፣ ደረቱን የደቃ

ሕዝብ ነው።” ያሉት ወንጌላዊ ያሬድ፣ “ የፍትሕ ዕጦትና የመድልዎ ብሶት አንገሽግሾት የሚሰማኝ መንግሥት አለ በሚል አደባባይ ቢወጣ እንደ እባብ ተቀጥቅጧል፣ ተዋክቧል፣ ታስሯል፣ ተሰዷል፣ ተገድሏል። ለዚህ እውነታ ማስረጃ ማቅረብ

የሚገባኝ አይመስለኝም፤ እርሶም አጥርተው እንደሚያውቁት አልጠራጠርም።” ብለዋል።

አሁንም ጊዜው ሳይመሽ ፖለቲካዊ መፍትሔዎች ላይ እንዲተኮር፣ የኃይል እርምጃው እንዲቆም፣ ተዓማኒ እርምጃዎች እንዲወሰዱና ሌሎችንም ያሳተፈ አገራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቻላቸውን እንዲያደርጉ ወንጌላዊ ያሬድ ጠይቀዋል።

“ይህንንም ማድረግ ካልቻሉ ግን…” ይላሉ ወንጌላዊ ያሬድ ደብዳቤያቸውን ሲያጠቃልሉ  “ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን ከሚፈሰው የንጹሐን ደም እጅዎን እንዲያነጹ ሰውን በመልኩና በምሳሌው በፈጠረ በሕያው እግዚአብሔር ስም እማጸኖታለሁ።”