ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ያዋቀሩት አዲሱ ካቢኔ የኦሮሚያና የአማራ ህዝብ የጠየቃቸውን ጥያቄዎች የማይመልስ መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (ጥቅምት 23 ፥ 2009)

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ማክሰኞ ያዋቀሩት አዲሱ ካቢኔ የኦሮሚያና የአማራ ህዝብ የጠየቀውን የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ እና የማንነት ጥያቄዎችን የማይመልስ እንደሆነ ተገለጸ። ለረጅም አመት በስራ ላይ የነበሩ የመንግስት ባለስልጣናት ተሸጋሽገው ስልጣን ከመያዛቸው ውጭ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተነሱ ህዝባዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ  የተለየ እርምጃ አለመውሰዱን የተለያዩ አካላትን ዋቢ ያደረጉ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ኮርትዝ (Quartz) የተሰኘው የዜና ድረ-ገጽ እንደዘገበው፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ህዝባዊ ተቃውሞ ሲያደርጉ የነበሩ ዜጎች፣ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ባደረጉት የካቢኔ ሽግሽግ ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልጾ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር የኦህዴድ አባላት ሹመት በኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ እንደማያመጣ ገልጿል።

ዶር ነገሪ ሌንጮ የኦህዴድ አባል መሆናቸውን የገለጸው ይኸው ኮርትዝ ድረ-ገጽ፣ ባለስልጣኑ ታማኝ ካድሬ እንደሆኑ ገልጿል። የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ለህወሃት እጅግ ቅርበት ያላቸው ሰው መሆናቸው ማፕልክሮፍት (MapleCroft) የተሰኘ አማካሪ ድርጅትን ሃላፊዎችን ዋቢ በማድረግ ኮርትዝ ዘግቧል።

አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በተወካዮች ምክር ቤት ያስጸደቁት የካቢኔ ሽግሽግ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ህዝባዊ እምቢተኝነት አድራጊዎች ላይ ተፅዕኖ እንደማይኖረው በዚሁ ድርጅት ውስጥ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ኤማ ጎርደን (Emma Gordon) ዋቢ በማድረግ በድረገጹ ላይ አስፍሯል። በመሆኑም አቶ ሃይለማሪያም ያቀረቡት የካቢኔው ሽግሽግ የህዝባዊ ተቃውሞ አድራጊዎችን ፍላጎት በትንሹ እንኳን ያላሟላ እንደሆነ ተገልጿል።

በኦሮሚያና በአማራ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት “ጥልቅ ተሃድሶ” እያደረግኩኝ ነው ቢልም፣ ከዚህ በፊት የአስተዳደር በደል ሲያደርሱ የነበሩ ባለስልጣናት ቦታ መቀያየር እንጂ አዲስ ነገር አለመፈጠሩን ኢትዮጵያውያን እየገለጹ ነው።  የመልካም የአስተዳደር ጉድለት ያለባቸው፣ በህዝብ ላይ በደል ያደረሱና  በሙስና የተዘፈቁ ባለስልጣናት አሁንም በስልጣን ላይ ሆነው መገኘታቸው ህዝባዊ ቁጣን ከማባባስ ውጪ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞውን እንደማያበርደው እየተገለጸ ይገኛል።