ኢሳት (ሚያዚያ 11 ፥ 2009)
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ረቡዕ በወቅታዊ የሃገሪቱ ጉዳዮች ዙሪያ ለውጭና ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች ሊሰጡ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰረዘ። ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ግን መግለጫ መስጠታቸው ተዘግቧል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ለተጋበዙ ጋዜጠኞች ባሰራጨው አስቸኳይ መልዕክት የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ቀድሞ በተያዘለት ፕሮግራም እንዳማይካሄድ አስታውቋል። ይሁንና ጽ/ቤቱ መግለጫው በሌላ ጊዜ እንደሚካሄድ ቢገልፅም የረቡዕ ፕሮግራም በምን ምክንያት ሊሰረዝ እንዳቻለ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረቡዕ ከጋዜጠኞች ጋር ያደርጉታል ተብሎ በተጠበቀው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ማክሰኞ ለፓርላማ ቀርቦ የነበረው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ዋነኛ ትኩረት ሊሆን ይችል እንደነበር ጋዜጣ አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ለፓርላማ ከማቅረቡ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከቢቢሲ ጋር ባካሄዱት ቃለ-መጠየቅ መንግስት በህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ የሞቱና የታሰሩ ሰዎች ጉዳይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከአውሮፓ ህብረት ለቀረበ ገለልተኛ የማጣራት ጥያቄ ተባባሪ እንዳማይሆን ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሃምሌ 2008 አም ጀምሮ እስከ መስከረም 2009 አም ድረስ በአማራ፣ ኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች ተቀስቅሶ ከነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ 669 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽኑ ጥናቱ ከሃምሌ እስከ መስከረም ወር የተሸፈነ መሆኑን ቢያመለክትም፣ መንግስት ከሃምሌ ወር በፊት ከተቃውሞ ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ገለጾ እንደነበር የሚታወስ ነው።
አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ፈጽመውታል የተባለው የሃይል ዕርምጃ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር አይዘነጋም።
ይሁንና መንግስት ምርመራው በመንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተቋም እንደሚያካሄድ ምላሽን በመስጠት የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል።
ይኸው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ሃሙስ ለፓርላማ ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድበትና እንደሚያጸድቅ ለመረዳት ተችሏል።