ጥቅምት ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚ ሀይለማርያም ዛሬ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ መንግስት የጎዳና ላይ ነውጥ ከሚያሰቡት ሀይሎች ጋር ለመነጋገር የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
አቶ ሀይለማርያም በተቃዋሚዎች በኩል የሚቀርበው ቅጥ ያጣ ፍረጃ እና የጥላቻ ፖለቲካ እንዲቆም እንዲሁም የጎዳና ላይ ነውጥ እናደርጋለን በማለት የሚያስቡ ሀይሎችም ሀሳባቸውን እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። “የጎዳና ላይ ነውጥ ለማስነሳት በቂ መረጃ አለን ስንል “መንግስት ፈርቶ ማስፈራራት ጀመረ” እንባላለን ያሉት አቶ ሀይለማርያም፣ ይህ መንግስት አይፈራም፣ ታሪኩም ባህሪውም እንደዛ አይደለም ብለዋል። ይህ መንግስት ፈርቷል እያላችሁ እራሳችሁን አታሞኙ፣ መንግስት አይፈራም የህዝብ መንግስት ነው ፣ ኳሱ እናንተ እጅ ላይ ነው” ብለዋል።