ኢሳት (ሃምሌ 5 ፥ 2008)
በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ቁጣ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ኤፈርት ንብረት የሆነው ሰላም ባስን ጨምሮ የንግድ ተቋማት መቃጠላቸው ተሰምቷል። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ እጅ አልሰጥም በማለት መታኮሳቸው የታወቀ ሲሆን፣ ከጎንደር ከተማና አካባቢም በርካታ ነዋሪዎች ዕርሳቸውን ለመታደግ ተንቀሳቅሰዋል።
በከተማዋ ሙሉ በሙሉ የንግድ እንቅስቃሴ ሆነ ስራ የቆመ ሲሆን፣ ኮ/ል ደመቀ ዘውዴን ለመታደግ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች በ6 አውቶቡሶች ወደጎንደር መንቀሳቀስ የጀመሩ ሲሆን፣ ከተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ህዝብ ድጋፉን ለመግለጽ ወደ ጎንደር በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ ተሰምቷል። ራቅ ባሉ አንዳንድ የአማራ አካባቢዎችም በየአካባቢው እንቅስቃሴ መታየት መጀመሩን ለኢሳት የደርሰው ዜና ያስረዳል።
ሃሙስ ማለዳ በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰውን ይህንኑ ግጭት ተከትሎም በርካታ የመንግስትና የግል አገልግሎት መስጫ ተቋማት የተዘጉ ሲሆን የጸጥታ ሃይሎችና የነዋሪው ፍጥጫ ምሽት ድረስ መቀጠሉ ታውቋል።
የከተማዋ ህዝብ በከፍተኛ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ውስጥ ይገኛል ያሉት እማኞች ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ እስከ ሃሙስ ምሽት ድረስ በመኖሪያ ቤታቸው ተከበው እንደሚገኙ ለኢሳት አስረድተዋል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ወልቃይት ወረዳ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች የተነሳውን የማንነት ጥያቄ ተከትሎ የወልቃይት ጠገዴ ኮሚቴ አባላትን በተደጋጋሚ ሲያስሩ መቆየታቸው ይታወሳል።
የመንግስት ባለስልጣናት ከማህበረሰቡ የተነሳው የማንነት ጥያቄ እልባት አግኝቷል ቢሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄያቸው ህጋዊ ምላሽን አለማግኘቱንና ውጥረቱ ተባብሶ መቀጠሉን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ማክሰኞ ማለዳ በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በአርማጭሆ ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች ወደ ጎንደር ከተማ በማቅናት ላይ መሆናቸውን የተለያዩ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከከተማዋ ወደ ትክል ድንጋይና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚወሰድ መንገድ የተዘጋ ሲሆን፣ ሰላም ባስ የተባለ አውቶቡስ ሙሉ ለሙሉ በእሳት ቃጠሎ መውደሙንም ከስፍራው ከተገኙ የፎቶና የቪዲይ ምስሎች ለመረዳት ተችሏል።
ማክሰኞ ማለዳ በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ በተመለከተ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስት እስካሁን ድረስ በቀጥታ ስለጉዳዩ የሰጡት መግለጫ የለም።
ሆኖም በአካባቢው ግጭት መኖሩን ግጭቱም ከኤርትራ ሃይሎች ጋር እንደሆነ መንግስት መግለጫ ሰጥቷል።