(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 7/2011) በኢትዮጵያ በክልሎች መካከል የሚነሱ ግጭቶችንና በማንነት ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮችን በዘላቂነት መፍታት በሚያስችል መልኩ ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወሰነ።
በተመሳሳይ የብሄራዊ እርቅና ሰላም ኮሚሽን እንዲቁቁምም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመወሰን ሁለቱንም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመራቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶችን አጣርቶ እልባት ለመስጠት የሚቋቋም ነው።
ተግባሩም እውነት እና ፍትህን መሰረት በማድረግ እርቅን ለማውረድ የሚያግዝ መሆኑ ነው የተገለጸው።
የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ደግሞ በሀገር አቀፍም ሆነ በክልሎች ጉዳዩ ላይ በሚነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ መለስ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
ከወሰን አስተዳደር ጋር ተያይዞ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል የቅራኔ ምንጭ የሆኑ ችግሮችን ገለልተኛ በሆነ፣ ሙያዊ ብቃት ባለው እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ የሚያፈላልግ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።
የኮሚሽኖቹ መቋቋም በኢትዮጵያ ያሉ መሰረታዊ የሚባሉ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል።
በተለይም ፍትህ ላጡና የተለያዩ በደሎች የደረሰባቸውን ወገኖች እንባ ለማበስ ያግዛል ነው የተባለው።
የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በዚህ ደረጃ ይቋቋማል ቢባልም የጉዳት ካሳን ስለመጨመሩ ግን የተነገረ ነገር የለም።
የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን መቋቋም ያስፈለገው ወልቃይት እና ራያን በመሳሰሉ አካባቢዎች የተነሱ የማንነት ጥያቄዎችን ለመፍታት ጭምር እንደሆነ መረዳት ተችሏል።
የሁለቱ አካባቢ ሕዝቦች ያለፈቃዳችን ወደ ትግራይ ክልል ተካለናል በሚል የአማራ ማንነት ጥያቄ ማንሳታቸው ይታወቃል።
የመብት ጥያቄ አራማጆቹን እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘወዱን ለመያዝ በተደረገ ሙከራ ግጭት ተቀስቅሶ በርካታ ሰዎች ለስደትና ለሞት መዳራጋቸው ይታወሳል።
በኦሮሚያና ሶማሊያ ክልሎች አጎራባች ወሰኖች በተነሳው ግጭትም በሺዎች ሲገደሉ እስከ አንድ ሚሊዮን ሰዎች መሰደዳቸው ይታወቃል።
አዋጆቹ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቁ በኋላ ሥራ ላይ ይውላሉ ተብሎ ይጠበቃል።