ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የሶስተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን ገለጠ

ጥር 21 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ንቅናቄው ለኢሳት በላከው መግለጫ ፤ በኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በውጭ አገራት ውስጥ በአፍሪቃ፣ በአውስትራሊያ፣ በሩቅና መካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አባሎቹ  ከጥር 12 ቀን እስከ 19 ድረስ ባደረጉት ሶስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የንቅናቀያቸውን ሪፖርቶች አዳምጠው በጥንካሬዎችና ድክመቶች ላይ ግልጽና ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጧል።

ግንቦት 7 ለኢትዮጵያዊያን ተስፋን የፈነጠቀ፤ በወያኔ ላይ ደግሞ ስጋትን ያሰፈነ ድርጅት መሆን ቢችልም ዘረኛውንና ግፈኛውን የመለስ ዜናዊን አገዛዝ ለማስወገድና በምትኩም ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈኑባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እስካሁን ከሠራው እጅግ የላቀ ሥራ መሥራት እንዳለበት መገንዘቡንም ንቅናቄው በመግለጫው አስፍሯል።

አገራችንና ሁሉንም የሃገሪቱን ዜጋ ከዘረኛው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ነፃ የማውጣትና ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈኑባት ሃገር የመገንባት ከፍተኛ ኃላፊነት በእኛ ትውልድ ላይ የወደቀ መሆኑን ተረድተናል የሚለው ግንቦት 7 ፣ አባላቱ ይህንን እውን ለማድረግ ህይወታቸውን ፣ ንብረታቸውንና ጊዜያቸውን ለትግሉ ለማዋል ቆርጠው መነሳታቸውን ገለጠዋል።

በዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ የፓለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማኅበራት ጋር በጋራ ለመሥራት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያጠናክርም ንቅናቄው አስታውቋል።

በመጨረሻም ግንቦት7 ኢትዮጵያውያን እንዲቃለቀሉት ጥሪ አቅርቧል።

በሌላ ዜና ደግሞ ጥምረት የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር የአመራር አባላት እና እውቁ የሰብአዊ መብቶች አቀንቃኝ የሆነው ታማኝ በየነ በሚገኙበት በዋሽንግተን ዲሲ ስብሰባ እንደሚአደርግ አስታውቋል።

ጥምረቱ ለኢሳት በላከው መግለጫ የግንቦት7 ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ እና ኦነግን በመወከል ቃሲም አባ ናሻ ፌብሩዋሪ 19፣ 2012 በዋሽንግተን ዲሲ ሼራተን ናሽናል ሆቴል ተገኝተው በወቅታዊ የፖለቲካና የትግል ስትራቴጂ፣ በዲሞክራሲ እና በነጻነት ዙሪያ  ከኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ያደርጋሉ።