ግንቦት 7 የመለስ መንግስት በኤርትራ ላይ የሰነዘረውን ጥቃት አወገዘ

መጋቢት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ የመለስ ሠራዊት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚደረገዉን የ ሰላም ጥረት በማደናቅፍና የአለም አቀፉን ህግ በመጣስ የኤርትራን ግዛት ወርሮ ማን አለብኝነት የተሞላበት ወታደራዊ ጥፋት መፈጸሙን አስታውሶ፣  ወታደራዊ ትንኮሳውና ጥቃቱ የአፍሪካን ቀንድ ከዚህ ቀደም ታይቶ ወደ ማይታወቅ ትልቅ የጦርነት እሳት ዉስጥ ሊከት የሚችል የጀብደኝነት ተግባር ነዉ ብሎታል።

የወያኔ አገዛዝ ይህንን የምስራቅ አፍሪካን አካባቢ የጦርነት እሳት ዉስጥ የሚጨምርና የአለምን ሰላም የሚያናጋ አሳፋሪ ወታደራዊ ጥቃት ከፈፀመ በኋላ ይህንኑ አሳፋሪ ድሪጊቱን ለአለም ህዝብ ያሳወቀዉ ትልቅ ገድል እንደፈፀመ ሰዉ በመኩራራት መሆኑ አገዛዙ ምን ያህል በጀብደኝነትና በማን አለብኝነት የተወጠረ እብሪተኛ አገዛዝ መሆኑን በግልጽ ያሳያል ብሎአል።

ኢትዮጵያናኤርትራ ከ1998 – 2000ድረስ ለሁለት አመታት የዘለቀ ጦርነትአካሂደው ህልቆ መሳፍርት ህዝብ እና ንበረት መውደሙን አወሳው ንቅናቄው አሁንም ተመሳሳይ ጥፋት ለመፈጸም የሚሯሯጠውን ወያኔን ከጠብ አጫሪነት ተግባሩ እንዲቆጠብ አለማቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግ ጠይቋል።

ባለፉት ሀያ አመታት ወያኔ እመራዋለሁ ከሚለዉ ህዝብ ጋርና ከጎረቤት አገሮች ጋር ጦርነት ዉስጥ መክረሙ በግልጽ የታየሀቅ ነዉ የሚለው ግንቦት7፣  የወያኔ አገዛዝ በየአቅጣጫዉ የሚያካሄደዉ ጦርነት ከአገር ጥቅምና ደህንነት ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ይልቁንም ወያኔ የጦርነት ከበሮ መምታት የሚጀምረዉ አገር ዉስጥ ከህዝብ የሚመጣዉን የነፃነት፤    የፍትህ ና የዲሞክራሲ ጥያቄ አቅጣጫ ለማስቀየርና የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ብቻ መሆኑን በተደጋጋሚ የወሰዳቸዉ ፀረህዝብ እርምጃዎች በግልጽ እንደሚያሳዩ ገልጧል።

ንቅናቄው በመጨረሻም ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛት፤ የቆዳ ስፋትና ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ አኳያ የምስራቅ አፋሪካን አካባቢ ሰላምና መረጋጋት በማስከበሩ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት መቻሏ የሚያጠራጥር አይደለም ካለ በሁዋላ፤ ሆኖም ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ አገዛዝ በዘረኝነትና በጠብ አጫሪነት ላይ የተመሰረተ እስከ ሆነ ድረስ ኢትዮጵያ የአካባቢዉ ሰለምና መረጋጋት መደፍረስ ዋነኛ ምክንያት መሆን እንደምትችልም መገንዘብ እንደሚያስፈልግም አውስቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጣሊያን መንግስት የኢትዮጵያ ጦር ወደ ኤርትራ ድንበር ዘልቆ በመግባት የፈጸመውን ጥቃት ኮንኖ መግለጫ አውጥቷል።

የጣሊያን መንግስት ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የመለስ መንግስትም የጣሊያንን መንግስት አቋም የሚተች መግለጫ ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ባወጣው መግለጫ ” የጣሊያን መንግሥት  የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችንና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እያሳሰበ ያለውን የኤርትራ ድርጊት በሚዛናዊነት ሳይመለከት ያሳየው ቀናነት የጎደለው አቋም በአካባቢው ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ላይ ገንቢ ሚና እንደሌለው ያመለክታል” በማለት ወቀሳ አሰምቷል።

ታዛቢዎች እንደሚሉት ደግሞ የመለስ መንግስት በጣሊያን ላይ ያወጣው የአቋም መግለጫ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሀል የሚሉት አይነት ነው ይላሉ። የመለስ መንግስት በኤርትራ ላይ ጥቃት የፈጸመው ራሱ መሆኑን በይፋ አስታውቆ እያለ፣ አሁን መልሶ ጥቃት እንዳልፈጸመ አድርጎ አለምን ለማሳመን የሚያደርገው ጥረት ፣ የጅል ዲፕሎማሲ የሚያራምድ ያስመስልበታል በማለት ታዛቢዎች ይናገራሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide