ግንባታቸው የተስተጓጎለው ፋብሪካዎች ወደ ግንባታ የሚገቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከህንድ ባለስልጣናት ጋር ምክክር እያካሄዱ መሆኑ ታወቀ

ኢሳት (ሚያዚያ 18 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች የተመራ የልዑካን ቡድን ግንባታቸው ተስተጓጎሎ የሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ግንባታ የሚገቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከህንድ ባለስልጣናት ጋር በሃገሪቱ ምክክር እያካሄዱ መሆኑ ታወቀ።

የህንድ መንግስት ኮርፖሬሽኑ ሊያካሄዳቸው ላቀዳቸው 10 የስኳር ፋብሪካዎች ማስጀመሪያ ከአራት አመት በፊት የ600 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል።

የህንድ መንግስት ለፋብሪካዎቹ ግንባታ ካቀረበው ብድር በተጨማሪ በርካታ ሰራተኞች በፕሮጄክቶቹ እንዲሰማሩ ቢያደርግም ፋብሪካዎቹ አሁንም ድረስ ምርት ማምረት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሃገሪቱ ፋብሪካዎቹን ወደ ስራ ለማስገባት በያዘችው ዕቅድ ዙሪያ እና በኢትዮጵያ የስኳር ኢንስቲትዩት መቋቋም በሚቻልበት ዙሪያ ለመምከር በስኳር ኮርፖሬሽን አማካሪ አቶ መንግስስትአብ ገብረኪዳን የተመራ የልዑካን ቡድን በህንድ የካንፑር ከተማ ምክክር እያካሄደ መሆኑን ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

ይኸው የልዑካን ቡድን አሁን በሃገሪቱ ያሉ የሰባት ስኳር ፋብሪካዎችን ቁጥር ወደ 17 ከፍ ለማድረግ በመንግስት በኩል እቅድ እንደተያዘ ማብራሪያን አቅርቧል።

ይሁንና መንግስት ለተጨማሪ የስኳር ፋብሪካዎቹ ግንባታ ለህንድ መንግስት የብድር ጥያቄ ስለማቅረቡ እስካሁን ድረስ የተሰጠ መረጃ የሌለ ሲሆን የህንድ ባለስልጣናት በዘርፉ የጀመሩን ድጋፍ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳሳዩ ጋዜጣው በዘገባው አስፍሯል።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከህንድና ከቻይና መንግስታት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ወስዶ ግንባታቸው የተጀመረው የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ስራ ባይገቡም ብድር የመክፈያው ጊዜ ግን መቅረቡ ሲገለፅ ቆይቷል።

ከህንድ በተገኘ ብድር ግንባታው ተጀምሮ የነበረው ተንዳሆን ስኳር ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቋም ቢባልም ለፋብሪካው ግብዓት የሚያገለግል የሸንኮራ አገዳ እጥረት በማጋጠሙ ፋብሪካው እስከቀጣዩ አመት ድረስ ስራ እንደማይጀምር ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ከወራት በፊት በአማራ ክልል ለተቋቋመው የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ያስፈልጋል ተብሎ የተተከለ የሸንኮራ አገዳ ፋብሪካው ከመጠናቀቁ በፊት ደርሷል ተብሎ ምርቱ እንዲወገድ መደረጉን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በዚሁ ድርጊት በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ መድረሱም በወቅቱ ተገልጿል።

ሃገሪቱን ስኳር ላኪ ያደርጓታል ተብለው የነበሩት እነዚሁ የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ስራ ባለመግባታቸው ምክንያት መንግስት ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ሲሆን፣ ስኳርን ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ እየተመደበ መሆኑ ተመልክቷል።

መንግስት አጋጥሞት ያለውን ይህንኑ ችግር ዕልባት ለመስጠት ከህንድ መንግስት ጋር በመምከር የስኳር ኢንስቲትዩት ለማቋቋም ፍላጎት እንዳለው የህንዱ ጋዜጣ ዘግቧል።

በሃገሪቱ ጉብኝትን እያደረጉ ያሉ የስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች ኢንስቲትዩቱን ለማቋቋም የህንድን ድጋፍ እንደጠየቁም ታውቋል።

ሊቋቋም የታሰበው ኢንስቲትዩት ለፋብሪካዎቹ የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ያለመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ የህንድ ባለሙያዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ የስኳር ፕሮጄክቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኮርፖሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች ለፋብሪካዎቹ የሚያስፈልግ በቂ የሰው ሃይል በሃገር ውስጥ አለመኖሩን ለህንድ ባለስልጣናት መገልጻቸውንም ታይስም ኦፍ ኢንዲያ ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል። የህንድ ብሄራዊ የስኳር ኢንስቲትዩት ሃላፊ የሆኑት ናሬንድራ ሞሃን ከልዑካን ቡድኑ ጋር ስምምነት እንደሚፈጸም ለጋዜጣው ገልጸዋል።