ግብፅ የአባይ ግድብን በተመለከተ ሱዳንን ያሳተፈ ድርድር እንዲካሄድ ጠየቀች

ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2009)

ግብጽ በተያዘው ወር በአዲስ አበባ ከተማ ከሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በፊት ሱዳንን ያሳተፈ የአባይ ግድብ ድርድር እንዲካሄድ ጠየቀች።

በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባትን ተከትሎ በሁለቱ ሃገራት መካከል በአባይ ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረ ድርድር መቋረጡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጀርባ ግብፅ እጇ አለባት ሲሉ ቅሬታን ማቅረባቸው በሰፊው ሲዘገብ ቆይቷል።

ይህንኑ አለመግባባት ተከትሎም ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያደሰውን ተፅዕኖ እንዲያጠኑ የተመረጡ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ወደ ስራ መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል።

የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳምህ ሹክሪ በነዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ኢትዮጵያ በተያዘው ወር ከሚካሂደው የአፍሪካ ህብረት ልዩ የመሪዎች ጉባዔ በፊት ስብሰባን እንድትጠራ መጠየቃቸውን አህራም የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

ሚኒስትሩ በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ሱዳን ተሳታፊ እንድትሆን ለኢትዮጵያ አቻቸው ዶር ወርቅነህ ገበየሁ ሃሳብ ማቅረባቸውንም ጋዜጣው አስነብቧል።

ማክሰኞ የስልክ ንግግር አካሄደዋል የተባሉት ሁለት ሚኒስትሮች በሃገራቸው መካከል ተፈጥሮ የሚገኘውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻልም መምከራቸው ታውቋል።

የግብፅ መንግስት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እያቀረበች ላለው ቅሬታ ይፋዊ ምላሽን ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን በቅርቡ ገልጾ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ይኸው ጉዳይ በሶስትዮሽ መድረክ ዋነኛ መወያያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የግብፅ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ በኩል የተቃውሞ አባላትን (በተለይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን) ትደግፋላችሁ ሲባል የቀረበባቸውን ቅሬታ ከእውነት የራቀ ሲሉ ያስተባብላሉ።