ኢሳት (ታህሳስ 10 ፥ 2009)
የሳውዲ አረቢያ ከፍተኛ ባለስልጣናት የአባይ ግድብ ፕሮጄክት መጎብኘታቸውን ተከትሎ ግብፅ ድርጊቱ “አደገኛ” ነው ስትል ተቃውሞን አቀረበች።
የሳውዲ አረቢያ ንጉስ ሰልማን አማካሪ የሆኑት አህመድ አል-ካቲብ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ እና ሳውዲ አረቢያን ግንኙነት በሚጠናክረበት ዙሪያ በአዲስ አበባ ጉብኝንትን ማድረጋቸው ይታወሳል። በሃገሪቱ የሶስት ቀን ቆይታ የነበራቸው አል-ካቲብ በአባይ ግድብ ያልተጠበቀና ቀድሞ ባልተያዘ ፕሮግራም ጉብኝት ማድረጋቸውን የግብፅ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የሳውዲ አረቢያው ባለስልጣን በግድቡ ያደረጉት ጉብኝት 92 ሚሊዮን አካባቢ የሚደርሰውን የግብፅ ህዝብ ጥቅም የሚጎዳና አደገኛ አካሄድ ነው ሲሉ የቀድሞ የሃገሪቱ የመስኖ ሚኒስትር መሃመድ ናስሩዲን ለጋዜጠኞች መግለጻቸውን ኢጂብት ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ሰኞ ዘግቧል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር ምክክርን ያካሄዱት የሳውዲ አረቢያው ከፍተኛ ባለስልጣን በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ስምምነት መድረሳቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ባለፈው ሳምንት ዘግበው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
ግብፅ ከሩሲያ ጎን በመቆም በሊቢያ እየተካሄደ ላለው የሃገሪቱ ወታደራዊ ዕርምጃ የሰጠችው ድጋፍ ከሳውዲ አረቢያ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲሻክር ያደረገ ሲሆን፣ ሁለቱ ሃገራት በአለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ባላቸው አቋም ግንኙነታቸው እየቀዘቀሰ እንደሄድ ማድረጉ ይነገራል።
ግብፅና ሳውዲ አረቢያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የሳውዲ ባለስልጣናት ግብፅ ስጋት አለኝ በምትለው የአባይ ግድብ ግንባታ ጉብኝት ማድረጋቸው ግንኙነታቸው ይበልጥ እንዲሻክር ማድረጉን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
ይሁንና የሳውዲ አረቢያ ከግብፅ ለቀረበበት ተቃውሞ እስካሁን ድረስ የሰጠችው ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ሃገሪቱ ከዚሁ ፕሮጄክት የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለየመንና ለሱዳን እንዲቀርብ እገዛ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት ለመርዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጉብኝት ላደረጉ የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናት ሃገራቸው የአባይ ግድብ ግንባታን በማገናዘብ እንድትደግፍ ጥያቄን ማቅረባቸውም ተመልክቷል።
ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያላቸውን ልዩነት ለመፍታት በርካታ ምክክርን እና ድርድርን ቢያካሄዱም እስካሁን ድረስ የመተማመን ስምምነት መድረስ አልቻሉም።
ከዚሁ የግድብ ግንባታ ዜና ጋር በተገናኘ በኦሞ ወንዝ ላይ ግንባታው ሲካሄድ የቆየው የግልገል ጊቤ ሶስተኛው የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ቅዳሜ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት መዋሉ ታውቋል።
1ሺ870 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም ያልው ይኸው ፕሮጄክት ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ 60 በመቶ የሚሆነው ወጪው ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር መሸፈኑን ዘ-ኢስት አፍሪካን የተሰኘ መጽሄት ዘግቧል።
አስር አመትን እንደፈጀ የተነገረለት ይኸው ሃይል ማመንጫ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል ለሃገር ውስጥና ለጎረቤት ሃገራት እንደሚቀርብ ተነግሯል።