ኢሳት (ነሃሴ 17 ፥ 2008)
በመገባንት ላይ ባለው የአባይ ግድብ ዙሪያ ላለፉት አራት አመታት ተቃውሞን ስታቀርብ የቆየችው ግብፅ በመካሄድ ላይ ያሉ ድርድሮች ስጋቷን እየቀነሰላት እንደመጣ አስታወቀች።
በድርድሩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡት የግብፅ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ ሃገራቸው ከአሁን በሁዋላ የምትፈራው ነገር እንደሌለ ለግብፅ መገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል።
ሁለቱ ሃገራት ግድቡ በገለልተኛ አካል ጥናት እንዲካሄድበት እያደረጉ ያለው ድርድር ለሁሉም ወገኖች ማረጋገጫ የሰጠ ነው ያሉት ፕሬዚደንት አል-ሲሲ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ የፕሮጄክት ስምምነት እንደሚፈረም መግለጻቸውን አል-አህራም የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ አስነብቧል።
የአባይ ወንዝ ለሁሉም ተፋሰስ ሃገራት ፍሰቱን ይቀጥላል ሲሉ ፕሬዚደንቱ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ወር በገለልተኛ አካል የሚያካሄደው ጥናት ማሻሻያ እንዲያደርግበት ከተፈለገ ማሻሻያውን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ለግብፅ የማረጋገጫ ፍንጭ መስጠቱ ይታወሳል።
ይህንኑ ተከትሎ በግድቡ ላይ ማብራሪያን የሰጡት ፕሬዚደንት አል-ሲሲ ሃገራቸው የነበራት ስጋት እየቀነሰ መምጣቱን ለህዝባቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት አራት አመታት ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ስለማይኖር ምንም አይነት ማስተካከያ አይደረግበትም ሲል አቋሙን ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል።
ይሁንና ይህ አቋም በምን ምክንያት ሊቀየር እንደቻለ ዝርዝር መግለጫን ያልሰጡ የውሃና ኤነርጂ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ጥናቱን ተከትሎ ማሻሻያ ማድረግ ከተፈለገ ጉዳዩ እንደሚታይ በቅርቡ ይፋ አድርገዋል።
ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለማጥናት የተመረጡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና ግብፅ ከኩባንያዎቹ ጋር በመስከረም ወር ላይ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ኩባንያዎች ይፋ የሚያደርጉት የጥናት ውጤት ይግባኝ የሌለው እንዲሆን ከዚህ በፊት በካርቱም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።