ግብፅ ለኢትዮጵያ ስደተኞች የምትሰጠው ድጋፍና ከለላ ፖለቲካዊ አይደለም አለች

ኢሳት (መጋቢት 28 ፥ 2008)

የግብፅ መንግስት በሃገሪቱ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ስደተኞች እየሰጠ ያለው ድጋፍና ከለላ ፖለቲካዊ ትስስር የሌለው መሆኑን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎረቤት ሃገራት ለኢትዮጵያ ስደተኞችን አሳልፈው መስጠት መጀመራቸውን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ግብፅና ሌሎች ሃገራት በመግባት ላይ መሆናቸውን አል-ሞኒተር የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

ሃገሪቱ ለኢትዮጵያውን ስደተኞች እየሰጠች ያለችው ድጋፍም አለም አቀፍ ህጎችን መሰረት ያደረገ እንደሆነና ፖለቲካዊ ይዘት የሌለው መሆኑን የግብፅ የስደተኞች ድጋፍ ፋውንዴሽን ሃላፊ የሆኑት አህመድ ባዳዊ ገልጸዋል።

ለሌላ ሃገራት ስደተኞች ከሚደረገው ድጋፍ በተለየ መልኩም ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች የተለየ ነገር እየተደረገ አለመሆኑንም ሃላፊው ከጋዜጣው ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።

በቅርቡ በመዲናይቱ ካይሮ የተካሄደን ከፍተኛ የኦሮሞ ማህበረሰብ ዝግጅት ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚገኙ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ግብፅ የኦሮሚያን ክልል ተቃውሞ ትደግፋለች የሚል ዘገባን እያቀረበ እንደሆነ አል-ሞኒተር ጋዜጣ የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ይሁንና፣ በጉዳዩ ዙሪያን ምላሽን የሰጡት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃላፊዎች ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚደረገውን ድጋፍ በማውሳት ጉዳዩ ፖለቲካዊ ትስስር እንደሌለው ገልጸዋል።

በቅርቡ በካይሮ ለተካሄደው የኦሮሞ ማህበረሰብ ዝግጅትም በሃገሪቱ ደንብ መሰረት ለስነ-ስርዓቱ የጸጥታ ጥበቃ ከማድረግ ያለፈ ግብፅ ምንም አይነት ጉዳይ እንደሌላት ስማቸውን  መግለጽ ያልፈለጉ ባለስልጣናት ለጋዜጣው አስታውቀዋል።

በግብፅ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽንም የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ በመያዝ ለሌላ ሃገር ስደተኞች የሚደረገውን ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ባለስልጣናቱ አክለው አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ከአምስት አመት በፊት ሟች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግብፅ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችንና ሰርጎ ገቦችን ትደግፋለች ሲሉ የሰጡትን መግለጫ በማውሳት ዘገባዎችን እያቀረቡ እንደሚገኝ አል-ሞኒተር ጋዜጣ አስነብቧል።

ይህም ጉዳይ ለኢትዮጵያና ግብፅ መካከል መነጋገሪያ ጉዳይ እየሆነ የመጣ ሲሆን፣ የግብፅ ባለስልጣናት ስደተኞቹን የማስጠለሉ ተግባር ፖለቲካዊ ተልዕኮ የሌለው እንደሆነ አስታውቀዋል።

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ መግለጫን አውጥቶ የነበረው የግብፅ መንግስት ችግሩ የውስጥ ጉዳይ ነው ሲል መግለጹ ይታወሳል።

ጎረቤት ኬንያና ሱዳን ወደ ሃገራቸው የተሰደዱ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያ አሳልፈው ሲሰጡ መቆየታቸውን የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲቃወሙት መቆየታቸውም የሚታወቅ ነው።