ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በሀራቸው ላይ ያቀረበችውን አማጽያንን የመርዳት ክስ አጥብቀው አስተባብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ትናንት ሀሙስ ባደረጉት በዚሁ ንግግራቸው መንግስታቸው የኢትዮጵያ አማጽያንን እና ተቃዋሚዎችን ደግፎ እንደማያውቅና ይህንን የማድረግ ሀሳብም እንደሌለው መግለጻቸውን አሶሲየትድ ፕሬስን የጠቀሰው የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ያመለክታል።
ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ እየተካሄደ ያለውን ግዙፍ የአኤልክቲሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ እንደማትቃወም የጠቀሱት ፕሬዚዳንት አል ሲ ሲ፤ ምክንያቱም ግንባታው ሀገራችን ከአባይ ወንዝ ላይ ማግኘት ያለባትን ታሪካዊ ጥቅም ያስጠበቀ ነው ብለዋል።
አል ሲሲ በዚህ ንግግራቸው የአባይ ጉዳይ ለግብጻውያን የህይወትና የሞት ጉዳይ ነው ብለዋል። እንደ ዋሽንግተን ፖስት ዘገባ 92 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት በረሀማዋ ግብጽ የግብርና ምርቷና የመጠጥ ውሃ አቅርቦቷ በአባይ ወንዝ ላይ የተመሰረተ ነው። ኢትዮጵያ፣ አሸባሪ ብላ ለፈረጀችው ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር ግብጽ ስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ እየሰጠች እንደሆነ ማስረጃ አለኝ በማለት ክስ ያቀረበችው ባለፈው ሰኞ ነው።
የኢጥዮጵያ መንግስት ግብጽ ላይ ክስ ባቀረበበት በዚሁ መግለጫው በምስል ካቀረባቸው ሁለት የቪዲዮ ማስረጃዎች አንዱ በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊም ብራዘር ሁድ መሪ መሀመድ ሙርሲና የቀድሞ የካቢኔ አባሎቻቸው የዛሬ አራት ዓመት የአባይ ግድብን እየተቃወሙ በግብጽ ቴሊቪዥን ያደረጉት ውይይት ነው።