(ኢሳት ዲሲ–ጥር 8/2010)
የግብጹ ፕሬዝዳንት ጄኔራል አብዱልፈታህ አልሲሲ ከሱዳንም ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት አንፈግም አሉ።
በአካባቢው የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ ፍላጎታችን ነው ያሉት ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ሀገራቸው በማንም ሀገር ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላትም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የሱዳን መንግስት በበኩሉ በግብጽና በኤርትራ መንግስት ላይ ያቀረበውን ክስ በመሳብ ጉዳዩን ከሱዳን መንግስት ተቃዋሚዎች ጋር አያይዞታል።
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ከሀገራቸው ቴሌቪዥን ጋር ትላንት ሰኞ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሀገራቸው ከሱዳንም ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ አስታውቀዋል።
“ከወንድሞቻችንም ይሁን ከማንም ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት አልፈልግም በማንም ሀገር ጉዳይ አናሴርም ጣልቃም አንገባም” ሲሉ ሀገራቸው ከአካባቢው ሀገራት ጋር ያላትን ጤናማ ግንኙነት ማስቀጠል እንደሚፈልጉ ተነግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ሱዳን በግብጽና በኤርትራ ላይ ስታቀርብ የነበረውን ክስና ወቀሳ ተከትሎ መግለጫ መስጠቷ ታውቋል።
ሰራዊቷን ወደ ኤርትራ ድንበር ያስጠጋቸው ከግብጽም ሆነ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ሳይሆን መሳሪያ የታጠቁ የሱዳን መንግስት ተቃዋሚዎችን በተመለከተ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር በሰጡት መግለጫ ሰራዊታችንን ወደ ከሰላ ያስጠጋነው አንዳንድ ተቃዋሚዎች በሀገራችን ምስራቃዊ ክፍል በመታየታቸው ነው ብለዋል።
ችግሩን ከየትኛውም ሀገር ጋር አላያያዝንውም፣የጸጥታም ስጋት ስላለብን ግን ወታደሮቹን አስጠግተናል ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ባለፈው ሳምንት የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ረዳት ኢብራሂም ሙሀመድ ከግብጽና ኤርትራ የሃገራቸውን ጸጥታ አደጋ ላይ የሚጥል መረጃ ደርሶናል ሲሉ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
የግብጽ ወታደሮች ኤርትራ ገቡ በሚል አልጀዚራ ያቀረበውን ዘገባ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው እሁድ ማጣጣላቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ ነገ ረቡዕ ካይሮ ግብጽ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።