ጥር ፭(አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር -በኢትዮጰያ እየተሰራ ያለው ግድብ የሚይዘው የውሀ መጠን በግብጽ የውሀ ድርሻ ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል እንደሚቃወመው አስታወቀ።
አህራም ኦንላይን “ሜና”የተሰኘውን የ አገሪቱን የዜና አገልግሎት ጠቅሶ እንደዘገበው በመስኖ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአባይ ግድብ ቃል አቀባይ የሆኑትን ሚስተር አላን ያሲን በአሁኑ ወቅት ኢየተሰራ ያለውና 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይይዛል የተባለው ግድብ ግብጽ የውሀ ድርሻ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚፈጥር በመጥቀስ፤ ኢትዮጰያ የግድቡን ውሀ የመያዝ አቅም እንድትቀንስ ጥሪ አቅርበዋል።
ቃል-አቀባዩ አቶ ያሲን ሀገራቸው ግብጽ እየተሰራ ባለው ግድብ ላይ ጥናት ማድረጓን በማውሳት ፤ <<ግድቡ በውሀ የመያዝ አቅሙ ፍትሐዊ ያልሆነና በቴክኒክ ረገድም ተቀባይነት የሌለው ነው>> ብለዋል። ባለፈው ጥቅምት ወር የ ኢትዮጰያ መንግስት ከግድቡ ሥራ 40 በመቶ ያህሉ እንደተጠናቀቀ መግለጹ ይታወሳል። የግድብ ግንባታውን በተመለከተ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ኢትዮጰያ፣ግብጽና ሱዳን የሶስትዮሽ ኮሚቴ ማቋቋማቸው ሲታወቅ፤ እስካሁን ባለው ሂደት ኮሚቴው ተስማምቶ እየሰራ እንደሆነ በ ኢትዮጰያ በኩል ሲገለጽ ቆይቷል።
“ሜና” የዜና አገልግሎት እንደዘገበው ግን ኮሚቴው በተያዘው የጥር ወር አጋማሽ ስብሰባ የሚቀመጥ ሲሆን፤ በስብሰባው ሀገራቱ የግድቡን ተጽእኖ አስመልክቶ ጥናት የሚያደርግ ዓለማቀፍ ተቋም ይመርጣሉ።
የግብጽ ባለስልጣናት ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ ግንባታው- በግብጽ የውሀ አቅርቦት ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ከባድ ጉዳት አስመልክቶ አስመልክቶ ከኢትዮጰያ መንግስት ጋር ውይይት ሊደረግባቸው የሚችሉ በርካታ የቴክኒክ ጉዳዮች አሉ ማለታቸው አይዘነጋም። እንደ ግብጽ ብሄራዊ ፕላን ኢንስቲትዩት እቅድ፤ ግብጽ- እስካሁን ድረስ ከአባይ ወንዝ ያላትን የውሃ አቅርቦት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከ 2050 ዓመተ ምህረት ድረስ በየ አመቱ በ21 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የማሳደግ እቅድ አላት።