ሐምሌ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት ምንጮች እንደገለጡት የመዝጊያው ጊዜ እስከዛሬ ድረስ ባልተለመደ ሁኔታ የተራዘመው ፓርላማ ፣ ነገ ረቡእ ለልዩ ስብሰባ ተጠርቷል።
በነገው ስብሰባ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ ይገኙ እንደሆን ለምንጫችን ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን ፣ “እስካሁን ድረስ ይገኛሉ የሚል ፍንጭ አለመሰማቱን፣ ይሁን እንጅ ይገኛሉ ብለው እንደማያስቡ” ተናግረዋል።
በፓርላማው አሰራር መሰረት አቶ መለስ በተገኙበት የሚቀጥለው አመት በጀት ለፓርላማው ተልኮ ከጸደቀ በሁዋላ፣ ፓርላማው ለእረፍት ይዘጋል። በነገው እለት ከሚቀርቡት አጀንዳዎች መካከል የበጀት ማጽደቅና የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ተሳትፎ የሚጠቁሙ አጀንዳዎች አልተካተቱም። በዚህም የተነሳ አሁንም በጀቱ መቼ እንደሚጸድቅ፣ አቶ መለስ መቼ ፓርላማ ላይ ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር እንደሚያድረጉ የፓርላማ አባላት አያውቁም። አንዳንድ የፓርላማ አባላት ለአፈጉባኤው ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ” ጥሪ ተጠባበቁ” የሚል መልስ ብቻ ማግኘታቸውን ለዘጋቢያችን ገልጠዋል።
ትናንት የአቶ መለስ ዜናዊን የጤና ሁኔታ በማስመልከት በሰራነው ዘገባ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ በደቡብ ሱዳን 1ኛ አመት የነጻነት በአል ላይ ይገኛሉ ተብሎ ቢጠበቀም፣ በእርሳቸው ቦታ ምክትላቸው አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
ፎርቹን ጋዜጣ “ፋይን ላይን” በሚለው አምዱ አቶ መለስን የጠየና ሁኔታ ዘገባ ይዞ ወጥቷል። ጋዜጣው አቶ መለስ ዜናዊ ያለፈውን ሳምንት ውጭ አገር ሄደው መታከማቸውንና አገር ውስጥ አለመኖራቸውን ገልጧል፡፤ እርሳቸው ወደ ለንደን እና ሌሎች አገሮች ተጉዘው የታከሙበትን ወጪ የገንዘብ ሚኒስቴር ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስተላላፉን፣ ሌሎች መስሪያ ቤቶችም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ህክምና ያወጡትን ወጪ እንዲያሳውቁ የተጠየቀበት ሰርኩላር ደብዳቤ እንዲታደግ መደረጉን ዘግቧል።
ፎርቹን ” የአቶ መለስ የቅርብ ሰዎች አቶ መለስ ክብደት የቀነሱት በቅርቡ የምግብ መቀነስ ወይም ዳይት በመጀመራቸው ነው” የሚል መልስ እንደሚሰጡ፣ የዲፐሎማቲክ ምንጮች በበኩላቸው ” ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ህክምናቸውን ጨርሰው በሙሉ ጤንነት ባለፈው ቅዳሜ ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን መናገራቸውን ” ጽፏል።
ጋዜጣው ህዝብ እየተነጋጋረ፣ የመንግስት ሰራተኞች እና ሌሎች ወገኖችም ጉዳዩን በአንክሮ እየተከታተሉት በመሆኑ መንግስት ወሬው ከቁጥጥር ውጭ ሳይወጣ፣ የመንግስት ፕሮፓጋንዲስቶች” አንድ ነገር እንዲሉ መክሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቀናት በፊት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የጫኑ 80 አውቶብሶች፣ እንዲሁም ከባድ መሳሪዎችን የጫኑ በርካታ ሎቤድ መኪኖች ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አቅንተዋል። በሰሜኑ አካባቢ ወታደራዊ ጥበቃውን ለማጠንከር ለምን እንደተፈለገ የታወቀ ነገር የለም።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide