(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 21/2010)በቅርቡ በኢሉባቡር ዞን በተፈጠረው ግጭት ለተፈናቀሉ ዜጎች ግሎባል አልያንስ የላከው ከግማሽ ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገንዘብ ለተፈናቃዮቹ እንዳይደርስ ተከለከለ።
በመላው አለም በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመታደግ የተቋቋመው አለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ግሎባል አሊያንስ የኢሉባቡር ተፈናቃዮችን ለመታደግ የላከውን 700 ሺ ያህል ብር ለማድረስ የሄዱት ሰዎች ያለውጤት አካባቢውን እንዲለቁ ተገደዋል።
በኢሉባቡር ዞን በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመታደግ አለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ግሎባል አሊያንስ የላከውንና 25ሺ የአሜሪካን ዶላር ወይንም 700ሺ የሚገመተውን የኢትዮጵያ ብር ለተፈናቃዮቹ ለማድረስ የተንቀሳቀሱት በሀገሪቱ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲ ተወካዮች መሆናቸው ታውቋል።
በመኢአድ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ በአቶ አዳነ ጥላሁን የተመራውና አራት አባላት የተካተቱበት የመኢአድና የሰማያዊ ፓርቲ ተወካዮች ገንዘቡን ለተፈናቃዮቹ ለማድረስ ኢሉባቡር ዞን መቱ ከተማ ከገቡ በኋላ ተፈናቃዮቹ ወዳሉበት እንዳይደርሱ መከልከላቸውን መረዳት ተችሏል።
ገንዘቡን ለተፈናቃዮቹ ለማድረስ ያደረጉት ሙከራ ባለመሳካቱ ከቀናት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ኢሳት ያገኛቸው የቡድኑ መሪ አቶ አዳነ ጥላሁን እንደተናገሩት የኢሉባቦር ዞን ሃላፊዎች ለቀናት ካስጠበቋቸው በኋላ እንደከለከሏቸው አስታውቀዋል።
ከክልሉ መንግስት ፈቃድ ሳትይዙ ተፈናቃዮችን ማግኘትም ሆነ እርዳታ ማድረግ አትችሉም መባላቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
በዚህም ለተፈናቃዮቹ እርዳታ ለማድረስ የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ግሎባል አልያንስ በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉትን ወገኖች ለመታደግ በአባገዳዎች በኩል ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው።